በመጪው የትንሳኤ በዓል ሁሉም የኤሌትሪክ ሀይል የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት 24 ሰዓት እንደሚሰሩ ተገለፀ

በበዓላት ወቅት ከሚኖረው ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት አኳያ ሊያጋጥም የሚችለውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መዋዠቅን ለመቀነስና ፤ ሲከሰትም አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በመጪው የትንሳኤ በዓል ሁሉም የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት 24 ሰዓት እንደሚያገለግሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታዉቋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሓይል አገልግሎት የኮርፖሬት ኮምኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ  ለብስራት እደተናገሩት ከበዓሉ ጋር ተይያዞ በኤሌክትሪክ መስመሩ ላይ ከፍተኛ የኃይል መጨናነቅ ሊከሰት ይችላል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ከዋናው መስመር ኃይል የሚያገኙ የከፍተኛና የመካከለኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች ከሚያዝያ 19 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ንጋት 11፡00 ሰዓት  ድረስ ኃይል ቀንሰው እንዲጠቀሙ አሳስበዋል፡፡

ጨምረውም ኤሌክትሪክ በሚቋረጥበት ጊዜ የጥገና ስራ ለማከናወን የተቋሙን መታወቂያ የያዙ ባለሞያዎቻችን በተለያዩ አካባቢዎች ሊንቀሳቀሱ ስለሚችሉ፤ ህብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር ያደርግ ዘንድ ጥሪ አቀርበዋል፡፡

ደንበኞች በቤት ውስጥ የሚገለገሉባቸውን ቁሳቁሶች ኃይል ቆጣቢና ለአደጋ የማያጋልጡ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ እና በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ሰው ሰራሽ አደጋዎች እንዳይከሰት ጥበቃ ያደርጉ ዘንድም ገልፀዋል፡፡

ቃልኪዳን ተስፋዬ