በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አራት የንግድ ማስተላለፊያ ኬላዎች ሊከፈቱ መሆኑ ታውቋል

በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ህጋዊ የድንበር ላይ ንግድ ልውውጥ ለማስጀመርና ለመቆጣጠር አራት የንግድ ማስተላለፊያ ኬላዎችን ለመክፈት ስራዎች መጠናቀቃቸውን በገቢዎች ሚኒስትር የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ አዲስ ይርጋ በተለይም ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡

ከሚከፈቱት ኬላዎች መካከል ሁለቱ በዛላምበሳና ራማ ሲሆኑ በሀገራቱ መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ሳቢያ ግንኙነታቸው ተቋርጦ ለሁለት አስርት ዓመታት መቆየቱ ይታወሳል፡፡

በሀገራቱ ዜጎች መካከል ድንበር ላይ የተጀመረው የንግድ ልውውጥ የጉምሩክ አሰራርን ጨምሮ ህጋዊ ስርዓት እንዳልተበጀለት ሲነገርም ቆይቷል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የዛላምበሳ ድንበር፤ የጉምሩክና ተያያዥ ስርዓቶች እስኪስተካከሉ ተብሎ በቅርቡ መዘጋቱ የሚታወስ ጉዳይ ነው፡፡

ይህንን ሁኔታ በመለወጥ የሀገራቱን የምጣኔ ኃብታዊና የንግድ ግንኙነት ህጋዊ በሆነ መንገድ ለማስቀጠል የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን እና  ህጋዊ የድንበር ላይ የንግድ ልውውጥ ሊጀመር መሆኑን አቶ አዲስ ጨምረው ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል፡፡

ፍሬህይወት ታደሰ