በጋብቻ ላይ ጋብቻ የፈፀሙት ጥንዶች በእስራት ተቀጡ

ተከሳሾች ባልና ሚስት ሲሆኑ 1ኛ ተከሳሽ ጄላን አማን እንዲሁም 2ተኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ሀቢባ ሁሴን ይባላሉ፡፡

ድርጊቱ የተፈፀመው የካቲት 13 ቀን 2011 ዓ.ም በሰበታ ከተማ ቀበሌ 04 ልዩ ቦታው ፉሪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡

የግል ተበዳይ ወ/ሮ ፈትያ ሀሰን ከ 1ኛ ተከሳሽ ጋር በትዳር ተጣምረው 1ድ ልጅ በጋራ አግኝተዋል፡፡

ተከሳሽ ወ/ሮ ሀቢባ ሁሴን ከተባለችው ሁለተኛ ተከሳሽ ጋር ሌላ ትዳር መስርቶ መኖር ይጀምራል ቀስ በቀስም እያመሸና እያደረ ይመጣል ፤ በዚህ ጥርጣሬ ውስጥ የወደቀችው ሚስት እግር በእግር ተከታትላ መጋባታቸውን ታረጋግጣለች፡፡

ከዚያም ክሱን በሰበታ ከተማ 3 ፖሊስ ጣቢያ ታስመዘግባለች፡፡

1ኛ ተከሳሽ ስለጉዳዩ ተጠርቶ ሲጠየቅ ድርጊቱን መፈፀሙን ያምናል 2ተኛ ተከሳሽ በበኩሏ ሚስት እንዳለው ስላልነገረኝ ጋብቻውን ፈፅሜያለው ትላለች፡፡

በዚህ ሁኔታ ፖሊስ ተጋብተው መኖር መጀመራቸውን በማረጋገጥና የምርመራ መዝገቡን አጣርቶ በማጠናቀቅ ለሰበታ ከተማ ፍርድ ቤት ይልካል፡፡

አቃቤ ህግ በመሰረተው በጋብቻ ላይ ጋብቻ የመፈፀም ክስ መሰረት ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋተኝነታቸው በመረጋገጡ ሚያዝያ 14 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት 1ደኛ ተከሳሽ 1ዓመት ከሁለት ወራት ፣ 2ተኛ ተከሳሽ ደግሞ በ 8 ወር እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን በሰበታ ከተማ ምክትል ኮማደር አደም ሀሰን በተለይም ለብስራት ተናግረዋል፡፡

ሚኪያስ ፀጋዬ