ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ ተጨማሪ ጥረት እና ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ይህ የተነገረው የጤናማ እናትነት ወር በአለም ለ30ኛ ጊዜ በኢትዮጲያ ለ13ኛ ጊዜ በባህርዳር እየተከበረ ባለበት ወቅት ነው፡፡

የዘንድሮው በዓል በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት በጋራ እንከላከል በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ስነ ስርዓቶች እተከበረ ይገኛል፡፡

የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ከጤና ኬላዎች እስከ ሆስፒታሎች በስፋት በመገንባት፣ እንዲሁም አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እስከ ስፔሽያሊስቶች በማሰልጠን ለእናቶች  የሚሰጠው የጤና አገልግሎት እንዲሻሻል መደረጉን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በተለይም ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ሌሎችም የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ እና ከሞት ለመታደግ የሚያስችሉ አስተዋፅኦዎችን በማበርከት ጥረቶች ማድረግ ይኖርባቸዋል ተብሏል፡፡

በየአመቱ የሚመዘገበው የእናቶች ሞት በፊት ከነበረው በከፍተኛ ቁጥር እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም አሁንም በአመት ከ 11ሺ እስከ 13ሺ የሚሆኑ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ህይወታቸው እንደሚያልፍ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በዚሁ ወቅት ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የእናቶች ሞት ምክንያት ከወሊድ ጋር እንደሚያያዝ ተገልጿል።

ስለሆነም ተጨማሪ ጥረት እና ቀጣይነት ያለው ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

የደም ልገሳን ልማድ በማድረግ ደም የሚፈሳቸው እናቶችን በደም እጥረት ከሚደርሰውን ሞት ለመታደግ ሁሉም ዜጋ ደም በመለገስ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ዶ/ር ሊያ ጨምረው ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል፡፡

ትግስት ላቀው