ዘመናዊ የአኩሪ አተርና የሽንብራ ግብይት በይፋ ተጀምረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አኩሪ አተርና ሽንብራ ወደ ዘመናዊ ግብይት ስርአት ለማስገባት በትናንትናዉ እለት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስተር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አራጋ ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር አሊሮ ኦፒየዉ፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባደር አምባሳደር ፍፁም አረጋ በተገኙበት ግብይቱ በይፋ ተጀምሯል፡፡

የኢትዮጲያ ምርት ገበያ የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት ከሚያከናዉናቸዉ ተግባራት መካከል የዉጭ  ምንዛሬን የሚያስገኝና ፤ በገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸውን ምርቶች ወደ ግብይት ስርአቱ በማስገባት አርሶ አደሩን፣ አቅራቢዎቹን፣ ላኪዎቹን ብሎም ሀገሪቱን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተነግሯል፡፡

በምርት ገበያው የ 100 ቀናት እቅድ አኩሪ አተርና ሽንብራን ወደ ግብይት ለማስገባት ተሰርቷል፡፡

ይህም የዘመናዊ ግብይት ስርአቱን ጠቀሜታ የተገነዘቡ አርሶ አደሮች በምርት ገበያው በኩል ግብይታቸውን እንዲያከናወኑ በተደጋጋሚ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው ሲሉ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር አሊሮ ኦፒየዉ ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል፡፡

በእለቱ ኢንጅነር ኦሊሮ ኦፒየዉ እንደገፁት ባለፉት አምስት አመታት በአማካይ በየአመቱ 439 ሺ ቶን ሽንብራ እና 76 ሺ ቶን አኩሪ አተር ለዉጭ ገበያ ቀርቧል፡፡

ለአብነትም በ 2010 ዓ.ም 1 መቶ 10 ሺ ቶን አኩሪ አተርና 49 ሺ ቶን ሽምብራ ለዉጭ ገበያ ቀርቦ በጠቅላላዉ ከ91 ሚሊየን ዶላር በላይ ተገኝቷል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ለብስራት ተናግረዋል፡፡

ቃልኪዳን ተስፋዬ