የጅማ ኢንደስትሪ ፓርክን ቴክኖሎጂ የሚጠቀም የቡና ማቀነባበሪያ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው ተባለ

ኢትዮጵያ ባለ ልዩ ጣዕም ቡና አምራች ሀገር ብትሆንም ቴክኖሎጂ የሚጠቀምና እሴት የተጨመረበት ቡና ለአለም ገበያ ስለማታቀርብ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም እያገኘች አይደለም መባሉን በኢኖቬሽን ሚኒስትር የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ አቶ ገብረእግዚያብሄር አሰፋ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡

ታጥቦ፣ ተቆልቶ፣ ተፈጭቶ እና ታሽጎ ያለቀለት ቡና በኤሌክትሮኒክ ግብይት ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን የቻይና ባለሃብቶች በዚህ ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀርቦላቸዋል ተብሏል፡፡

ከኢትዮጵያ ‹‹ያለቀለት›› ቡና ወደ ውጭ ለመላክ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት በቻይና ቤይጂንግ ተካሂዷል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ በቡና ሽያጭ ዘረፍ የተሰማሩ ድርጅቶች በተሳተፉበት በዚህ ውይይት የኢትዮጵያ መንግስት በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃቶች አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያርግ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አቶ አበበ አበባየሁ ተናግረዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ቡናን በኤሌክትሪኒክስ ግብይት ወደ ውጭ ከመላክ በዘለለ ደህንነቱ የተጠበቀ ግብይት ለመፈፀም የብሎክ ቼይን ቴክኖሎጂን ወደ ስራ ለማስገባት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ፍሬህይወት ታደሰ