መደበኛ ያልሆነ

ህፃን አርሴማ

በኩዌት የነበረችው ህፃን አርሴማ ወደ አገር ቤት ተሳፈረች፡፡
ህጻን አርሴማ የተወለደችው ወ/ሪት ፋጡማ ኤዶ ኮርኮሬ በምትባል ኢትዮጵያዊት ነው። እናቷ ከአሠሪዎቿ ቤት እያለች በገጠማት ችግር ምክንያት ከአሰሪዎቿ ቤት ወጥታ ወደኩዌት ያስመጣቻት የአሰሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ የሄደች ሲሆን በኤጀንሲዋ አማካኝነት ሆስፒታል ገብታ ከወለደች በኋላ ጉዳዩ በኩዌት ፖሊስ እየተጣራ እያለ ህፃንዋን በመተው ተሰውራለች።

የህፃኗ እናት ከጠፋችበት ጊዜ ጀምሮ በኩዌት ሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በተደረገ ፍለጋ አልተገኘችም።

በኤምባሲውም ፌስ ቡክ ላይ በተደጋጋሚ ማስታወቂያ በመለጠፍ፤ ልትገኝበት ትችላለች የተባሉ የመኖሪያ ቦታዎች እንዲሁም በኩዌት በርካታ ተከታይ ባላቸው ፌስ ቡክ ገጾች ላይ በሰፊው የማፈላለግ ጥረት ተደርጎ ልትገኝ አልቻለችም።

ህጻኗ አራት አመት የሞላት ቢሆንም በኩዌት የመኖሪያ ፈቃድ ስለሌላት ህክምናም ሆነ ትምህርት ልታገኝ አለቻለችም። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከኩዌት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች የኩዌት የመንግስት አካላት ጋር በመመላለስ ተደጋጋሚ ውይይት ተደርጎ ህፃን አርሴማ ወደአገር ቤት መሄድ እንድትችል ለማስፈቀድ ተችሏል።

በመሆኑም በኤምባሲው በኩል አስፈላጊው የጉዞ ሰነድ ተሟልቶላት ወደ ኢትዮጵያ እንድትሳፈር ተደርጓል። ወደ ኢትዮጵያው እንደደረሰች በማደጎ ህግ መሰረት አስፈላጊው ምዝገባ እንዲከናወን የሚደረግ መሆኑን እንገልጻለን።

ህፃን አርሴማን በማሳደግም ሆነ ወደ ሀገር ቤት የሚደረገው ጉዞ የተሳካ እንዲሆን በበጎ ፈቃደኝነት ሲተባበሩ ለነበሩ ዜጎቻችን ኤምባሲው ምስጋናውን አቅርቧል።

 

ምንጭ —-በኩዌት የኢትዮጵያ ኤምባሲ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *