የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ህብረት የሚኒስትሮች አስቸኳይ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር የአፍሪካ ህብረት የመዋቅር ማሻሻያ የህብረቱን የ2063 አጀንዳ ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ብስራት ሬድዮ ከውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ፅ/ቤት በተላከለት መረጃ መሰረት ማሻሻያው የስራ ድግግሞሽን በማስቀረት ህብረቱን ውጤታማ ለማድረግ ይረዳልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሴት ፕሬዘዳንት በቅርቡ መምረጧ እያካሄደችው ባለው ሁለገብ ማሻሻያ ውስጥ የሴቶችን እኩል ተሳትፎ ማረጋጋጥን ዋና አጀንዳ አድርጋ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡
በህብረቱም የሴቶችን እኩል ተሳትፎና ውክልና ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከስብሰባው በፊት ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ስምኦን ደረጄ