መደበኛ ያልሆነ

በመግደል ሙከራ የተከሰሱት ወንድምማማቾች በእስራት ተቀጡ

የወንጀል ድርጊቱ የካቲት 12 ቀን 2009 ዓ.ም ከምሽቱ 5፡00 አካባቢ በየካ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታዉ ጉራራ አደባባይ ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ መፈጸሙን በጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ በተለይም ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡

አግዘዉ ዘለቀና እዮብ ዘለቀ የተባሉ 1ኛና 2ተኛ ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም የወጣዉን የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ በመተላለፍ በፈፀሙት የመግደል ሙከራ ወንጀል የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

የግል ተበዳይ ሀብቶም አርአያን 1ኛና 2ኛ ተከሳሾች ጭንቅላቱ ላይ በዱላ ደጋግመው በመምታት በቀኝ በኩሉ ህብረ ሰረሰር ዉስጥ ጤናማ ያልሆነ የደም መፍሰስ፣ በግራ በኩል የአየር መግቢያና መዉጫ ቱቦ እንዲታፈንና እዲጎዳ፤ የአንገት ዉስጥ ጤናማ ያልሆነ ደም መፍሰስ እንዲያጋጥመዉና ለመራመድና ለመናገር እንዲቸገር፣ በአጠቃላይ የማገገም እድሉ እጅግ አነስተኛ እንዲሆን በማድረጋቸዉ በፈፀሙት የመግደል ሙከራ ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ከሳሽ የፌዴራል አቃቢ ህግ ተከሳሾች ወንጀሉን ስለመፈፀማቸዉ ያስረዱልኛል ያላቸዉን የሰዉና የሰነድ ማስረጃዎችን አያይዞ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡
ክሱን የተመለከተዉ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቦሌ ምድብ ወንጀል ችሎትም ተከሳሾች ጥፋተኛ ናቸዉ ሲል የቅጣት ዉሳኔዉን አስተላልፏል፡፡

በዚህም መሰረት ወንጀሉ በግብረ አበርነት የተፈፀመ መሆኑ እንደ አንድ የቅጣት ማክበጃ ተይዞ ህዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለዉ 2ተኛ የወንጀል ችሎት እያንዳንዳቸዉ በ6 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን አቶ ዝናቡ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡

 

ሚኪያስ ፀጋዬ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *