መደበኛ ያልሆነ

ባለፉት ስድስት ወራት ወደ አዲስ አበባ ከተማ የገቡ ከ2ሺ በላይ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች እና ከ50 ሺ በላይ ጥይቶች መያዙ ተሰማ

ከሀምሌ 1ቀን 2010 እስከ ታህሳስ 30 2011 ዓ.ም ባለው የስድስት ወር ጊዜ ብቻ በተደረገው ክትትል 2383 ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎች ተይዟል፡፡ከተያዙት የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች መካከል ሁለት የእጅ ቦንብና አንድ መትረየስ በተጨማሪም 56ሺ 615 ጥይት መያዙን የኮሚሽኑ ኢንዶክትሪኔሽንና ህዝብ ግንኙነት ም/ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ በተለይም ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል፡፡
የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎቹ የተሽከርካሪ አካል በመፍታትና ፣ የተሽከርካሪ አካል ላይ መሸሸጊያ በመስራት እንዲሁም ከሌሎች ዕቃዎች ጋር በማመሳሰል የጦር መሳሪያ ሲያዘዋወሩ ተይዘዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ በሚገኘው ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል በተሰራው ስራ ከ68 ሚሊዮን ብር በላይ ፣ 88ሺ 151 የአሜሪካ ዶላር ፣ 9ሺ 480 ዮሮ ፣ 12ሺ 620 ፓውንድ እና በርከታ የሌሎች ሀገራት ገንዘቦች ሊየዝ ችሏል፡፡

በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች አብዛኛውን ጊዜ ወንጀሉን የሚፈፅሙት በህጋዊ ንግድ ከለላ እንደሆነ እና አብዛኞቹ የስጦታ እቃ ፣ ቡቲክ ፣ ባርና ሬስቶራት የሚል ፈቃድ በማውጣት ህገ-ወጥ ተግባሩን ሲሰሩ እንደተያዙም ተገልጿል፡፡

ከህገወጥ የገንዘብ ዝውውር በተጨማሪ ሀሰተኛ የገንዘብ ዝውውር ላይ በተሰራው ስራ 163ሺ 600 ብር እና 3ሺ 800 የአሜሪካ ዶላር ሊያዝ ችሏል፡፡ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደለበት  እና በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ተሳትፎ ያደረጉ አካላት ከሁለት ሚለዮን ብር በላይ ለፖሊስ አባለት መደለያ ሲሰጡ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ኮማንደር ፋሲካ ጨምረው ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል፡፡

ሳምራዊት ስዩም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *