መደበኛ ያልሆነ

ሚያዝያ 3፣ 2012 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ተጨማሪ አራት ግለሰቦች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው፤ ከህመሙ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 10 ደርሷል።

በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 345 ግለሰቦች መካከል አራቱ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው መረጋገጡን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። ቫይረሱ ተገኝቶባቸው ክትትል እያደረጉ ከሚገኙት መካከል 10 ግለሰቦች አገግመዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፤ እስካሁን ባለው ሂደት በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለሶስት ሺህ 500 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተከናውኗል።

ዛሬ ቫይረሱ የተገኘባቸው አራቱም ግለሰቦች ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

ሁለቱ ወንድ ሁለቱ ደግሞ ሴቶች ሲሆኑ ሶስቱ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ናቸው።

ከእነዚህም መካከል አንድ የ30 ዓመት ሴትና አንድ የ29 ዓመት ወንድ ኢትዮጵያዊያን ከዱባይ መጥተው በለይቶ ማቆያ ክትትል ሲያደርጉ የነበሩ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

አንድ የ33 ዓመት ሴት ኢትዮጵያዊት ደግሞ የአሜሪካ አገር የጉዞ ታሪክ ያላት ናት።

ሌላኛው ግለሰብ የ42 ዓመት እድሜ ያለው ኢትዮጵያዊ ነው ብለዋል።

ግለሰቡ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ የሌለው ሲሆን፤ በህመሙ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንዳለውና እንደሌለው እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ ዜና ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጦ ክትትል እያደረጉ ከሚገኙ ግለሰቦች መካከል ተጨማሪ ስድስት ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸውን ሚኒስትሯ ይፋ አድርገዋል።

ይህን ተከትሎም በአጠቃላይ ከህመሙ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ወደ 10 ከፍ ብሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *