መደበኛ ያልሆነ

ግንቦት 27፣2012-የውጪ ሀገር ዜግነት ያለው ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ በመግባት ከ90 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ብር ፣ የአሜሪካ ዶላር እና የህንድ ገንዘብ ሰርቀው ለማምለጥ የሞከሩ ግለሰቦች እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል

ግንቦት 21ቀን 2012 ዓ/ም ለግንቦት 22 አጥቢያ ከለሊቱ 9 ሰአት ገደማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ለቡ ሙዚቃ ቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወንጀሉ መፈፀሙን የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ተወካይ ሀላፊ ዋና ሳጅን እሸቱ ቅጣው ገልፀዋል፡፡

ወንጀሉን ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩት 3 ግለሰቦች የህንድ ሀገር ዜጋ በሆነው የግል ተበዳይ ሰርኒ ቫሲን መኖሪያ ግቢ ውስጥ በአጥር ዘለው መግባታቸውን ያስረዱት ዋና ሳጅን እሸቱ የመኖሪያ ቤቱ መስኮት ክፍት ስለነበር በመስኮቱ በመግባት መኝታ ቤት ቁም ሳጥን ውስጥ በካዝና ተቀምጦ የነበረ 90 ሺህ 312 የኢትዮጵያ ብር 151 የአሜሪካ ዶላር እና 1215 የህንድ ገንዘብ(ሩፒ) መስረቃቸውን ተናግረዋል::

በተጨማሪም 9950 ብር ግምት ያላቸውን የተለያዩ አልባሳት ማህተም እና ቲተሮችን እንዲሁም ቼኮችን ሰርቀው መውሰዳቸውን ዋና ሳጅን እሸቱ ገልፀዋል::

ሶስቱ ተጠርጣሪዎች ወንጀሉን ሲፈፅሙ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ተኝተው የነበሩ ሰዎች ድምፅ ሰምተው በመንቃትና ለፖሊስ በመደወላቸው ፖሊስም ወደ ቦታው ፈጥኖ ደርሶ በአካባቢው ከነበሩ የጥበቃ ሰራተኞች ጋር በመተባበር ተጠርጣሪዎቹ ከግቢው ወጥተው ተደብቀው ለማምለጥ ሲሞክሩ እጅ ከፍንጅ ሊያዙ መቻላቸውን ዋና ሳጅን እሸቱ አስረድተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *