መደበኛ ያልሆነ

ሐምሌ 27፣2012-በቡርጂ ልዩ ወረዳ ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ከኦሮሚያ ክልል ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በሀገራዊና ክልላዊ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከቡርጂ ልዩ ወረዳ የህዝብ ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች የቡርጂ ህዝብ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ የሆነ ስጋት ውስጥ ሆኖ ነው ኑሮውን እየገፋ ያለው ብለዋል፡፡

በተለይ በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በታጣቂዎች አማካኝነት የአካባቢው ነዋሪዎች በመንገድ ላይ እና በእርሻ ስፍራዎች የግድያ እና ዘረፋ የወንጀል ተግባራት እየተፈጸመብን ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ልዩ ወረዳው ወደ ዞን እንዲያድግ ለመንግስት ጥያቄ አቅርበን ምላሽ አላገኘንም ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ ቀበሌን ከቀበሌ የሚያገናኝ መንገድ ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት እና ሌሎች መሠል የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች እንዲመለስላቸው ጠይቀዋል፡፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ከነዋሪዎቹ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ የደቡብን እና የኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ህዝቦችን እርስ በርስ በማጋጨት እና ቀጠናውን በመረበሽ የራሳቸውን ትርፍ ለማግኘት የሚጥሩ ሀይሎች እንዳሉ ተገንዝበናል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመነጋገር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

የአደረጃጃት ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ መንግስት ከህብረተሠቡ ጋር በመምከር ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል በማለት ማብራራታቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *