መደበኛ ያልሆነ

ነሐሴ 14፣2012-በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ከሰሞኑ በደረሰ የመሬት መንሸረታት አምስት የቤተሰብ አባላት ሕይወት አለፈ፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎንደር ዙሪያ ወረዳ ደብረሰላም ቀበሌ ከሰሞኑ በጣለው ከባድ ዝናብ በተፈጠረ የመሬት መንሸራተት አምስት የቤተሰብ አባላት ሕይወታቸው አልፏል፤ ሀብትና ንብረታቸውም በናዳው ጠፍቷል፡፡የተጎጂዎች ቤተሰብ ቄስ ዓለሙ ሞትባይኖር ለአብመድ እንደተናገሩት እህታቸው ከባለቤታቸውና ከሶስት ልጆቻቸው ጋር ሕይወታቸው አልፏል፡፡ናዳው በሌሊት በመከሰቱ ተጎጂዎች ሰው ሳይደርስላቸው እንደቀረ የተናገሩት ቄስ ዓለሙ እስከቤቱ ተደርምሶ እንደተገኙ ተናግረዋል፡፡ ሕይወታቸውን ያጡት ቤተሰቦች ሁለት ልጆቻቸው በወቅቱ ከቤት ስላልነበሩ ተርፈዋል ነው ያሉት፡፡ ልጆቹ አሁን ላይ ረዳት እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡

በመንግሥት በኩልም እስካሁን ድረስ መጥቶ ከማዬት የዘለለ ነገር የተደረገ ድጋፍ አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡ናዳው አምስት የቤተሰብ አባላቱን ከማጥፋቱም በላይ በአካባቢው ማኅበረሰብ ሰብል ላይ ገዱት ማድረሱንም ተናግረዋል፡፡አካባቢው ከአሁን ቀደም እንደዚህ አይነት አደጋ ተከስቶበት እንደማያውቅ ያስታወሱት ቄስ ዓለሙ እንደከዚህ ቀደሙ ምንም አይፈጠር በማለት እንደተዘናጉ ጉዳት እንደደረሰባቸው ነው የተናገሩት፡፡አሁንም በተራራው ግርጌ የሚኖሩ የማሕበረሰብ ክፍሎች በስጋት ላይ እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡ለማሕበረሰቡም ጊዜያዊ መጠለያ መዘጋጀት እንዳለበት ነው የተናገሩት፡፡ ዝናብ በዘነበ ቁጥር መደናገጥ እየተፈጠረ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *