መደበኛ ያልሆነ

ነሐሴ 26፣2012-የሳዑዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ ልዑል የመከላከያ ባለስልጣናትን ከስልጣን አነሱ

በየመን ጦርነት ተሳትፎ እያደረገ ከሚገኘዉ የሳዑዲ መራሹ ጥምር ጦር ከፍተኛ መሪ የሆኑት ልዑል ፋሃድ ቢን ቱርኪ ከስልጣን ተወግደዋል፡፡የልዑሉ ወንድ ልጅ ምክትል ገዢ የነበረዉ አብዱላዚዝ ቢን ፉሃድ ከስልጣን ተነስቷል፡፡

በተመሳሳይ በመከላከያ መስሪያ ቤት ዉስጥ ያልተገባ ከተባለ የፋይናንስ ዉል ጋር በተያያዘ አራት ባለስልጣናት ከስራ ተሰናብተዋል፡፡አልጋ ወራሹ ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን ከጸረ ሙስና ጋር የጀመሩትን ዘመቻ ተከትሎ ከፍተኛ ስራ እየሰሩ መሆናቸዉ ይነገራል፡፡

ሆኖም ግን ተቃዋሚዎቻቸዉን ለስልጣን እና ለአመራራቸዉ ያልተመቿቸዉን በሙስና በመወንጀል ያስራሉ ሲሉ ይተቿቸዋል፡፡በተያዘዉ የፈረንጆቹ ዓመት መጀመሪያ ላይ ብቻ ሶስት የንጉሳዉያን ቤተሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉ ይታወሳል፡፡

ለእስር የተዳረጉት የሳዑዲዉ ንጉስ ታናሽ ወንድም ልዑል አህመድ ቢን አብዱላዚዝ፣የቀድሞ አልጋወራሽ ልዑል ሞሃመድ ቢን ናይፍ ናቸዉ፡፡እ.ኤ.አ በ2017 ሪትዝ ካርልተን በተባለ ቅንጡ ሆቴል በርካታ የንጉሳዉያን ቤተሰብና ባለሀብቶች በቁጥጥር ስር እንዲዉሉ ማድረጋቸዉ አይዘነጋም፡፡

አብዛኛዎቹ ከእስር ሊለቀቁ የቻሉት በጥቅል ለሳዑዲ መንግስት 106.7 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ከከፈሉ በኃላ ነበር፡፡በአባታቸዉ ንጉስ አብዱላዚዝ መልካም ፈቃድ አልጋ ወራሽ ልዑል የተባሉት የ35 ዓመቱ ቢን ሳልማን በኢኮኖሚና ማህበራዊ በተለይም ሲኒማ ቤቶች እንዲከፈቱ ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ በመፍቀድ ተራማጅ ናቸዉ በሚል በርካታ ሽልማቶችን መቀዳጀት ችለዋል፡፡

ሆኖም ግን በተቀነባበረዉ የጋዜጠኛ ጀማል ካሾግጂ ግድያ፣ባልተሳከዉ የቀድሞ የሳዑዲ የደህንነት ሀላፊ የግድያ ሙከራ በየመን ቀዉስ ስማቸዉ በክፉ ይነሳል፡፡

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *