መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 7፣2013-የቦሌ አራብሳ ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች ውሃ ካገኙ አንድ ወር እንዳለፋቸው ተናገሩ

በቦሌ አራብሳ አካባቢ ውሃ ከመጣ ከአንድ ወር በላይ ማስቆጠሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለብስራት ሬዲዮ አቅርበዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ችግሩ ይፈታ ዘንድ በተደጋጋሚ ለአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን መ/ቤቱ ቅሬታቸውን ቢያቀርቡም ድርሻቸው በአካባቢው ለሚገኘው ለቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፖርክ መሰጠቱ እንደተነገራቸው አስረድተዋል፡፡

ብስራት ሬዲዮ በጉዳዩ ዙሪያ ለባለስልጣን መ/ቤቱ የኮሚኒኬሽን ባለሙያ ወ/ሮ ሰርካለም ጌታቸው ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን የመብራት መቆራረጥ ለችግሩ መንስኤ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አክለውም በቅሬታ አቅራቢዎቹ የተነሳው እና ድርሻችሁ ለቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ተሰጥቷል የሚለው መረጃ የሀሰት ወሬ ነው ብለዋል፡፡

ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ቦሌ አራብሳን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ውሃ ማዳረስ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

የለገዳዲ ማጣሪያ ጣቢያ ፕሮጀክትን ጨምሮ 7 የውሃ ጉድጋዶች በመብራት አለመኖር ምክንያት ስራቸውን በአግባቡ መስራት አለመቻላቸውን ያስረዱት ወ/ሮ ሰርካለም ፤ በመብራት ሃይል በኩል ያለው ችግር እንዲቀረፍ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ማቅረባቸውን ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡

ከቦሌ አራብሳ ነዋሪዎች በተጨማሪም በከተማዋ በሚገኙ አብዛኛው አካባቢዎች ላይ የውሃ አቅርቦት ችግር የማይፈታ ችግር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *