መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 4፤2013-በአዲስ አበባ ከተማ በመኪና ሽያጭ ላይ የተሰማራ ድርጅት ሁለት ተሸከርካሪዎችን ተዘረፈ

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው ልደታ ክ/ከተማ ልዩ ቦታው ብስራት ራዲዮ አካባቢ በመኪና ሽያጭ ላይ ከተሰማራው ያሬድ /ብስኩቴ/ መኪና መሸጫ በትላንትናው እለት ነው፡፡

ድርጅቱ በኤጀንሲ የተቀጠሩ ሁለት ጥበቃዎች ያሉት ሲሆን ከለሊቱ 10 ሰዓት የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ መኪኖች ተሰርቀዋል ፣ ጥበቃውም አብሮ ጠፍቷል የሚል መረጃን ለባለንብረቶቹ ያደርሳል፡፡

ከስፍራው የድርጅቱ ባለቤት አቶ ያሬድ እና ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ሲሳይ ሲደርሱ ከመሸጫ ግቢው ውስጥ የነበረ ዶልፊን ቶዮታ እንዲሁም ከደጃፍ ላይ ሌላ የቤት መኪና መወሰዱን ተመለከቱ፡፡

ተሸከርካሪዎቹ እንዲሁ ስለማይነሱ ቁልፍ የሚቀመጥበት በር ተገንጥሎ በጃምፐር አማካኝነት ተነስተው ሊወሰዱ መቻላቸውንና ባትሪም ይሁን ሌሎች እቃዎች በስፍራው እንደሚቀመጡ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ገልፀዋል፡፡

በስፍራው የነበረው ሌላኛው የጥበቃ ሰራተኛ ‹‹ምግብ አበሉኝ እንዲሁም መጠጥ አጠጥተውኝ ነበርና›› ደንዝዤ እንቅልፍ ሸለብ ስላደረገኝ ምን እንደተፈጠረ ኋላ ላይ ነው የተመለከትኩት የሚል ቃሉን ሰጥቷል፡፡

ጉዳዩን ለክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ያሳወቁ ሲሆን ፖሊስም የወንጀል ድርጊቱ ሪፖርት በተደረገለት ሰዓት ከስፍራው ደርሶ የማጣራት ስራ ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

ኮድ 3-A25899 አ.አ የሆነ ታርጋ ፈትተው መውሰዳቸውንም ነው አቶ ሲሳይ የነገሩን፡፡ በተጨማሪም ከመሸጫው ጎዳና ላይ ከሚቆሙት ተሸከርካሪዎች መሃከል ከአንደኛው የፊትና የኋላ ታርጋ ፈትተው መውሰዳቸውን ብስራት ራዲዮ ሰምቷል፡፡

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *