መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 10፣2013-በአፋር ክልል በ17 ወረዳዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ትምህርት ማስጀመር አልተቻለም ተባለ

የአፋር ክልል በጎርፍ በተጎዱ 17 ወረዳዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ ትምህርት ለማስጀመር እንደሚቸገር የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡

በክልሉ በጎርፍ አደጋ ምክንያት የተፈናቀሉ ከ67 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በ17 ወረዳዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

ተጎጂዎች ከትምህርት ቤቶቹ ለማወጣት መጠለያ እስካሁን ባለመዘጋጀቱ ትምህርት ቤቶቹን ከኮቪድ ጽዱ ለማድረግ ባለመቻሉ በተያዘለት ጊዜ ትምህርት ማስጀመር እንደማይችል የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ አህመዳየው ሰዲቅ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከታየው ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ በክልሉ በመድረሱ ችግሩ መከሰቱን በመጥቀስ ፤ በቀጣይ የመማር ማስተማር ሂደቱ ዙሪያ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከአደጋ ስጋት አመራር ቢሮ ጋር በመነጋገር ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ እስካሁን ግን መፍትሄ ተገኝቶ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉትን ዜጎች ማውጣት አለመቻሉን ጨምረው ነግረውናል፡፡

በአፋር ክልል የጎርፍ ፣ የኮሮና ወረርሽኝ እንዲሁም በአሁን ወቅት በሀገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ችግሮች እንዳሉም ሀላፊው ጠቁመዋል፡፡

መጠለያ ከሆኑት ትምርት ቤቶች ውጪ ሌሎቹ ዝግጁ መሆናቸውን በመግለፅ ፣ የአፍና የአፍንጫ ጭንብል የደረሳቸው ትምህርቱን እንደሚጀምሩ አቶ አህመዳየው ጨምረው ነግረውናል፡፡

ትግስት ላቀው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *