መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 14፤2013-በአማራ ክልል ትምህርት ተዘግቶባቸው በነበረባቸው ወቅቶች ፤ ከ 5ሺ በላይ እድሜቸው ለጋብቻ ያልደረሱ ህጻናት ተድረዋል ተባለ

በኮቪድ-19 ወረርሽኙ ምክንያት የመማር ማስተማሩ ተቋርጦ በነበረበት ወቅት ፤ በአማራ ክልል ከሚገኙ 92 ወረዳዎች ውስጥ ብቻ 5,763 እድሜቸው ለጋብቻ ያልደረሱ ህጻናት መዳራቸውን የክልሉ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል፡፡

በክልሉ በ9 ወራት ውስጥ ጋብቻ ከፈጸሙት 5,763 ሕጻናት መካከል አንድ ሺህ ስልሳ አንዱ ወንዶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ አራት ሺ ሰባት መቶ ሁለቱ ሴቶች መሆናቸውን በቢሮው የሴቶች ንቅናቄ ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ስማቸው ዳኜ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል፡፡

የ2013 የትምርት መርሀ ግብር ሲጀመር በወረዳዎቹ ከተዳሩት 3,919 የሚሆኑት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው አለመመለሳቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡

በሌሎች 100 ወረዳዎች እስካሁን ሪፖርት አለመድረሱን እና ቁጥሩ ከፍ ሊል እንደሚችል ከቢሮው ብስራት ሰምቷል፡፡

ከመጋቢት 2012 በፊት በክልሉ በድብቅ የተፈጸሙ ጋብቻዎች 161 ብቻ የነበረ ሲሆን ከመጋቢት ወር ወዲህ ቁጥሩ 5,763 መሆኑን አቶ ስማቸው ጨምረው ነግረውናል፡፡

ወደ ትምህርት ገበታቸው ያልተመለሱትን ተማሪዎች ለመመለስ በየወረዳዎቹ ከወላጆች ጋር ውይይት ተጀምሯል፡፡ እንዲህ አይነት ድርጊቶች ሲፈጸሙ በድብቅ ስለሚከወኑ መረጃዎችን ለማግኘት መምህራን እና ሌሎች የመንግስት ሰራተኞች ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑም ተጠቁማል፡፡

ትግስት ላቀው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *