መደበኛ ያልሆነ

የካቲት 15፤2013-ሃገር ውስጥ የሚገባ ዶላር በ 28 ቀናት ውስጥ እንዲዘረዘር የሚያስገድደው ህግ መሻሻል አለበት ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሞያዎች ገለጹ

የህጉ መሻሻል ወደ ሃገር ወስጥ የሚገባውን የዶላር መጠን ሊጨምረው እንደሚችልም ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡አሁን የሚስተዋለውን የዶላር እጥረት ለማሻሻል ዶላር ወደ ሃገር ውስጥ በገባ በ28 ቀናት ውስጥ እንዲዘረዘር የሚያስገድደው ህግ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ በሚፈልጉት ልክ ዶላር ይዘው እንዳይመጡ ያደርጋቸዋል ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሞያ እና የኢንቨስትመንት አማካሪ የሆኑት አቶ ያሬድ ሃይለመስቀል ገልጸዋል፡፡
ይሄ ቢያንስ በ28 ቀናት ውስጥ ዶላር መዘርዘር አለበት የሚለው አስገዳጅ ህግ ጊዜው እንዲራዘም ተደርጎ ቢሞከር ለውጡን መረዳት እንደሚቻል አቶ ያሬድ ይናገራሉ፡፡በሌላ መልኩ ምርቶችን ለውጪ ገበያ የሚያቀርብ ነጋዴ ያገኘውን ዶላር አጠራቅሞ ኢንቨስት እንዳያደርግም ይሄ ህግ መሰናክል እንደሚሆንበት አብራርተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ትምርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር አጥላው አለሙ በበኩላቸው የ 28 ቀን ህጉ መሻሻል እንዳለበት ሌላኛው ሃሳባቸውን ለብሰራት ሬድዮ የሰጡ ባለሙያ ናቸው፡፡ዶክተር አጥላው አለሙ እንደሚሉት በ 28 ቀናት ውስጥ ዶላር እንዲዘረዘር የሚያስገድደው ህግ ሰዎች በህገወጥ መንገድና በድብቅ በጥቁር ገበያ ዶላር እንዲዘረዝሩ መንገድ ከፍቷል ፡፡
ስለዚህም የዶላር እጥረቱንም ሆነ ህገወጥ ምንዛሬን ለመከላከል ህጉ መሻሻል እንዳለበት የምጣኔ ሃብት ባለሞያዎች ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡

ገነነ ብርሃኑ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *