መደበኛ ያልሆነ

ሰኔ 3፤2013-በአዲስ አበባ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት በአማካኝ 16 ደቂቃ ይወስዳል ተባለ

በመደበኛ የስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ 3 ሰዓት እንዲሁም ከምሽት ከ11 ሰዓት እስከ 1 ሰዓት ድረስ ለተከታታይ 5 ቀናት በየ10 ደቂቃ ልዩነት የአማካኝ የቆይታ ጊዜውን ለማወቅ በትራንስፖርት ባለስልጣን ጥናት ተካሂዷል።

በዚሁም መሰረት የሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አውቶቡሶች የመነሻና የመድረሻ የቆይታ ጊዜ በአማካኝ 13፡08 ደቂቃ ሲሆን አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት አውቶቡሶች ደግሞ 18፡09 ደቂቃ መሆኑ በጥናት ለማወቅ ተችሏል

የሁለቱ ድርጅቶች ጥቅል አማካይ የቆይታ ጊዜ 15 ደቂቃ ከ58 ሰኮንዶች መሆኑ በባለስልጣኑ የትራንስፖርት መረጃና ሲስተም ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኃይለማርያም ተ/ሚካኤል ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል

ጥናቱ ያካተተው በሸገር፣ በአንበሳ የከተማ አውቶቡስ እንዲሁም ከድጋፍ ሰጭዎች በናሙናነት በተመረጡ 24 መነሻና መድረሻ ተርሚናሎች ሲሆን፤ በጥናት በተለዩት መስመሮች ከፍተኛ የሕዝብ ትራንስፖርት ፍላጎት ያለባቸው፣ ረዥም የጉዞ መስመሮች፣ ረጃጅም ሰልፎች የሚታይባቸው አካባቢዎች ላይ የተካሄደ ነው፡፡

ጥናቱን ለማካሄድ ያስፈለገበት ዋንኛ ምክንያት በአዲስ አበባ በተጨባጭ የሚታየውን የህዝብ ትራንስፖርት አቅርቦትና ፍላጎት ያለበትን ክፍተት ለመሙላት፣ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማስቀመጥ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚታዩባቸውን መስመሮች በመለየት የመፍትሄ ሀሳብ ለመስጠት እንደሆነ ተጠቁሟል።

የትራንስፖርት መረጃና ሲስተም ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኃይለማርያም ተ/ሚካኤል በጥናቱ የተገኙ ግኝቶች ለህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ገልፀው፤ በቀጣይ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን በቴክኖሎጂ መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የሚስተዋለው የመንገድ መዘጋጋት፣ በከተማው በብዙሃን የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማሩት የግል ባለሀብቶች በአክስዮን ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ መሆናቸው እና መሰል ችግሮች ለቆይታ ጊዜ መራዘም በዋናነት የሚነሱ መሆናቸውን አቶ ሃይለማሪያም ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

ቤተልሄም እሸቱ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *