መደበኛ ያልሆነ

ሰኔ 3፤2013-በእድሳት ላይ የሚገኘው የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በመስከረም ወር ለተመልካች ክፍት ይሆናል ተባለ!

በእድሳት ላይ ያለፉትን አራት ወራት የቆየው ቴአትር ቤቱ በአሁን ወቅት የመጀመሪያው ምዕራፍ የግንባታው ሂደት ተጠናቆ ወደ ሁለተኛዋ ምዕራፍ የግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱልከሪም ጀማል በተለይ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

የጣራ እና የግድግዳ የግንባታው ስራ መጠናቀቁን ኃላፊው ተናግረዋል። የአዳራሽ ወንበር ፣ መጋረጃ እና የመድረክ ጀርባ ስራዎች ግንባታ የሚቀሩ ሲሆን ለወንበር እና ለፊኒሺንግ ስራ ጨረታ መውጣቱን ከሶስት ወራት በኃላ መላው የግንባታ ሂደት ተጠናቆ ለተመልካች ክፍት ይሆናል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ከነበረው በይበልጥ አሁን ላይ በዘመናዊ መልክ የሚገጠሙት የመጋረጃ እንዲሁም የመብራት ስራዎች ከውጪ የሚመጡ እንደመሆናቸው በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ከቻሉ ቴአትር ቤቱ ለአዲስ አመት ስራ ይጀምራል።

ቴአትር ቤቱ ለተመልካች ክፍት በሚሆንበት ወቅት ከዚህ ቀደም በተመልካች ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፉ ሆኖም ብዙ ጊዜ ያልታዩ እንዲሁም አዳዲስ ስራዎች የተካተቱበት አንድ ሙዚቃዊ ተውኔት እና ሁለት የአዘቦት ተውኔቶች ለተመልካች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ቴአትር ቤቱን በሚገነባበት ወቅት በርካታ ችግሮች ሲያጋጥሙት መቆየታቸውን የተናገሩት አቶ አብዱልከሪም በዋናነት የሲሚንቶ እጥረት፣የዲዛይን መለዋወጥ ስራው እንዲጓተት ማድረጉን አቶ አብዱልከሪም ጀማል ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

በቤቴልሄም እሸቱ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *