መደበኛ ያልሆነ

ሰኔ 4፤2013-የቡድን ሰባት አባል ሀገራት መሪዎች የዓለም የጤና ድርጅት በኮሮና ቫይረስ መነሻ ዙሪያ አዲስ ምርመራ እንዲካሄድ ጥሪ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል

በዩናይትድ ኪንግደም አስተናጋጅነት በዛሬዉ እለት የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ጉባዔ በደቡብ ምዕራባዊ የባህር ዳርቻ ኮርንዌል ይጀመራል፡፡የስብሰባው አፈትልኮ የወጣ ረቂቅ መግለጫ እንዳመለከተው ከሆነ የቡድን ሰባት አባል ሀገራት መሪዎች የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስ አመጣጥ ላይ አዲስና ግልጽ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ ያደርጋሉ ይላል፡፡

ጥሪው እንዲቀርብ እንቅስቃሴ የተጀመረው በጆ ባይደን አስተዳደር ሲሆን የድንገተኛዉ ወረርሽኝ መነሻ ምንድን ነዉ የሚለዉን የአሜሪካ የስለላ ተቋማት ምርምርን ለማስፋት ባይደን ያልተጠበቀ ውሳኔን አሳልፈዋል፡፡

ለዚህ መነሻ የሆነዉ ደግሞ በዉሃን የቪሮሎጂ ኢንስቲትዩት ላብራቶሪ ዉስጥ የሚሰሩ ሶስት ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዉ ህክምና ያገኙ ሲሆን ቫይረሱ ከመታወቁ ከአንድ ወር በፊት ያጋጠመ ስለመሆኑ ዎልስትሪት ጆርናል ከአሜሪካ የደህንነት ተቋም አፈትልኮ ወጣ ባለዉ መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡

ሆኖም ግን በጣሊያን ሚላን የካንሰር ኢንስቲትዩት የኮሮና ቫይረስ መቀስቀሱ በታህሳስ 2019 ከመታወቁ አስቀድሞ አንዳንድ ሰዎች በመስከረም 2019 በዚሁ ቫይረስ ተጠቅተዉ ህክምና አግኝተዋል፡፡

የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ዛሬ በሚጀምረዉ ጉባኤ በቫይረሱ መነሻ ዙሪያ ከሚያቀርቡት ጥሪ በተጨማሪ 1 ቢሊየን ዶዝ ክትባት ለመላዉ ዓለም ለማዳረስ ቃል ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተጨማሪ ለዲሞክራሲ ማበብ ስጋት ሆናለች ስለሚሏት ሩሲያ፣የቻይና የመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት ፍሰት በአዉሮጳ መጨመር እንዲሁም በአየር ንብረት ለዉጥ ዙሪያም ይመክራሉ፡፡

ከስብሰባዉ አስቀድሞ ባሳለፍነዉ እሮብ ዩናይትድ ኪንግደም የደረሱት ጆ ባይደን የመጀመሪያ ይፋዊ የስራ ጉብኝታቸዉን እያካሄዱ ሲሆን የፊታችን እሁድ ከንግስት ኤልዛቤት ሁለተኛ ጋር በማስከተል የኔቶ ስብሰባ በስተመጨረሻም በጄኔቫ ከሩሲያዉ አቻቸዉ ቭላድሚር ፑቲን ጋር ይመክራሉ፡፡

አሜሪካና ሩሲያ በበርካታ ጉዳዮች እየተወዛገቡ የሚገኝ ሲሆን ባይደን ከሞስኮ ጋር መልካምና የተረጋጋ ግንኙነት እንፈልጋለን ነገር ግን ሩሲያ ጎጂ ተግባር ዉስጥ ከሆነች ትርጉም ያለዉ የአጸፋ ምላሽ እንሰጣለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *