መደበኛ ያልሆነ

ጷግሜን 5፤2013-የህክምና ፍቃድ ሳይኖረው የኮቪድ -19 ህክምና ማዕከል በመክፈት አገልግሎት እየሰጠ የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

ተጠርጣሪው ግለሰብ በቁጥጥር ስር የዋለው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ የህክምና ፍቃድ ሳይኖረው ክሊኒክ በመክፈት የኮሮና ቫይረስ ህክምና ለተለያዩ ሰዎች ሲሰጥ ነው፡፡

የአየር መንገድ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ከቦሌ ክፍለ ከተማ የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ባለሙያዎች ጋር በሰሩት ጥናት ፍቃድ ሳይኖረው ክሊኒክ በመክፈት የኮሮና ቫይረስ ህክምና አገልግሎት ሲሰጥ የነበረውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወንጀል ምርመራ ክፍል የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በክፍለከተማው የወረዳ 2 የምግብ እና መድሀኒት ቁጥጥር ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጦና እንደተናገሩት ግለሰቡ ምንም አይነት የህክምና ፍቃድ ሳይኖረው በራሱ ተነሳሽነት በከፈተው የህክምና ማዕከል የውጪ ሃገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች ጭምር ህክምና ፈልገው መምጣታቸውን ገልፀው ነርስ ነን የሚሉ ግለሰቦችም በቦታው ላይ የህክምና አገልግሎት ሲሰጡ የተገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ በርካታ መድሀኒቶች በቤቱ ውስጥ የተገኙ ሲሆን ለምን አይነት ህመም የሚያገለግሉ መድሃኒቶች እንደሆኑም በማጣራት ላይ እንደሚገኙ ሀላፊው ገልፀዋል።

ህገ-ወጥ አገልግሎት የሚሰጡ አካላትን ለህግ አሳልፎ ከመስጠት አኳያ ህብረተሰቡ የሚያደርገው ትብብር መልካም የሚባል እና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መጠቆሙን ብስራት ሬዲዮ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *