መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 7፤2014-ፈረንሳይ ክትባት ያልወሰዱ 3ሺ የጤና ሠራተኞችን አገደች

በፈረንሣይ 3,000 የሚሆኑ የጤና ሠራተኞች የኮቪድ -19 ክትባት ባለመዉሰዳቸዉ የተነሳ ከስራ ታግደዋል፡፡ባሳለፍነዉ እሮብ በሥራ ላይ በዋለዉ አዲስ ሕግ መሰረት በፈረንሳይ ለ2.7 ሚሊዮን የጤና ባለሙያዎች፣ የቤት ለቤት እንክብካቤ እና የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞች ክትባት መዉሰድ አስገዳጅ ሆኗል።

ሆኖም ግን የፈረንሳይ የጤና ሚኒስትር ኦሊቪዬ ቬራን ሐሙስ እንዳሉት አብዛኛዉ እገዳው ጊዜያዊ ብቻ ነው ብለዋል።ደንቡ ለሁሉም ዶክተሮች ፣ ነርሶች ፣ ለሆስፒታል ሠራተኞች እና በጎ ፈቃደኞች አስገዳጅ ነዉ፡፡ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ስለ ደንቡ አስቀድመዉ በሰጡት መመሪያ ቢያንስ እስከ መስከረም 5 አንድ ዙር ክትባቱን መዉሰድ አልያም ከሥራቸው መልቀቅ እንዳለባቸው አስጠንቅቀዋል፡፡

ፈረንሳይና ጣሊያን ክትባት መዉሰድን አስገዳጅ ካደረጉ ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ግሪክ በበኩሏ ከተያዘዉ ሳምንት አንስቶ ስራ ላይ ባዋለችዉ ደንብ መሰረት ክትባት ያልወሰዱ የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ሠራተኞች በራሳቸው ወጪ የኮቪድ ምርመራን በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ማድረግ የግድ ይላቸዋል፡፡

በሚኪያስ ፀጋዬ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *