መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 13፤2014-አልጄሪያ የሞሮኮ በረራዎች የአየር ክልሏን እንዳይጠቀሙ አገደች

የአልጄሪያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀዉ የሀገሪቱ የአየር ክልል ለሁሉም የሞሮኮ ሲቪል እና ወታደራዊ አውሮፕላኖች ዝግ ስለመሆኑ ይፋ አድርጓል፡፡ይህ እርምጃ ሊወሰድ የቻለዉ በሞሮኮ በኩል በጥላቻ የተሞላ እና ጸብ ጫሪ ቀስቃሽ ድርጊት በመቀጠሉ የተነሳ እንደሆን ጽህፈት ቤቱ ባወጣዉ መግለጫ አስታዉቋል፡፡

አልጄሪያ ከሞሮኮ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በይፋ ማቋረጧ ይታወሳል፡፡የአየር ክልሏን ለሞሮኮ መዝጋቷን አልጀርስ ያስታወቀችዉ በፕሬዚዳንት አብዱልመጂድ ተቡቡኔ የሚመራዉ ከፍተኛ የፀጥታው ምክር ቤት ካካሄደዉ ስብሰባ በኃላ ነዉ፡፡

እርምጃው ሞሮኮን ከቱኒዚያ ፣ ከቱርክ እና ከግብፅ ጋር የሚያገናኟትን ሳምንታዊ 15 በረራዎች ላይ ብቻ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የሮያል ማሮክ አየር መንገድ አስታዉቋል፡፡በሮያል ማሮክ አየር መንገድ ላይ የሚሳድረዉ ተጽእኖ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም በሜዲትራኒያ ላይ በረራዎች እንዲደረጉ ያስገድዳል፡፡

ሞሮኮ እስራኤል ሰራሽ በሆነዉ የስለላ ቴክኖሎጂ ፔጋሰስ አልጄሪያ ባለስልጣናትን ትሰልል ነበር እንዲሁም በአልጄሪያ ለተቀሰቀሰዉ ሰደድ እሳት እጇ አለበት በሚል ትከሰሳለች፡፡ሞሮኮ ክሱን ዉድቅ በማድረግ የአልጄሪያ መንግስት የሞሮኮ ተገንጣይ ሀይሎችን ያስታጥቅብኛል ስትል በተራዋ ትወነጅላለች፡፡

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *