መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 14፤2014-በምስራቅ ወለጋ ዞን 29 ንፁሃን መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ !

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በምስራቅ ወለጋ ዞን ፣ ኪራሙ ወረዳ የሚገኙ ሲቪል ሰዎች ለደህንነታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆናቸው አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል።

በወረዳው ቦቃ ቀበሌ ከሚባለው ስፍራ ፣ መስከረም 7 እና 8 2014ዓ.ም በደረሱ 3ተያያዥ ጥቃቶች በአጠቃላይ 18 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል። እንዲሁም መስከረም 8 ቀን በውልማይ ቀበሌ በተፈፀመው ሌላ ጥቃት 11 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ አሳውቀዋል ነው የተባለው።

በኪራሙ ወረዳ ባለው አሳሳቢ የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ከተለያዩ የወረዳው አካባቢዎች ተፈናቅለው ፣ በኖሌ ቀበሌ በሀሮ እና ኪራሙ ከተሞች ተጠልለው የሚገኙ ከ 40 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ለወራት አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እና ሌሎች ድጋፎችን ባለማግኘታቸው አስቸጋሪ ሀኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ነዋሪዎች ጨምረው መግለፃቸውን ብስራት ራዲዮ ሰምቷል፡፡

በዚህ ወቅት ኪራሙ ወረዳ ከቡሬ እና ነቀምቴ ከተሞች ጋር የሚያገናኙ ዋና ዋና መንገዶች ፣ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ተዘግተው እንደሚገኙ ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡

ኢሰማኮ ፣ የፌደራልና የክልል መንግስታት የጸጥታ ሃይሎች በኪራሙ ወረዳ ላለው የፀጥታ ስጋት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እና በነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት የሚያደርሱ ሃይሎችን ከህግ ፊት ለማቅረብ ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲወስዱ አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም በግጭቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቀደመ ቀያቸው መመለሱ እንደተጠበቀ ሁኖ ተፈናቃዮች ለከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ከመጋለጣቸው በፊት በአፋጣኝ ወረዳውን ከአጎራባች አካባቢዎች የሚያገናኙ መንገዶች እንዲከፈቱና ፣ አስፈላጊው ሰብዓዊ እርዳታ መድረሱን እንዲያረጋግጡ ኪሚሽኑ በጥብቅ አሳስቧል፡፡

ሚኪያስ ፀጋዬ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *