መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 25፤2014-ህንድ በኮቪድ 19 ለተመዘገበ ለእያንዳንዱ ሞት 674 ዶላር ካሳ እንድትከፍል ተወሰነ

የህንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮቪድ -19 ምክንያት ለተመዘገበዉ ለእያንዳንዱ ሞት 50 ሺህ ሩፒ ወይም 674 ዶላር ለመክፈል የቀረበዉን የመንግስትን ውሳኔ አጽድቋል፡፡የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ያሳለፈዉ በሕንድ የአደጋ አስተዳደር ሕጎች መሠረት ካሳ እንዲከፈል በጠበቆች በኩል የቀረበዉን አቤቱታ ተከትሎ ነው።

ህንድ እስካሁን ድረስ ከ447ሺ በላይ የኮቪድ -19 ሞት ተመዝግቦባታል፡፡ሆኖም የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ በወረርሽኙ ህይወታቸዉን ያጡት ሪፖርት ከተደረገዉ በአስር እጥፍ እንደሚበልጥ ይናገራሉ፡፡

በትላንትናዉ እለት ዳኛ ኤምአር ሻህ የሟቹ ዘመድ ይህንን ካሳ በጠየቁ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ክፍያዉ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱ አክሎ እንደገለጸው አንድ ቤተሰብ ማመልከቻ ካቀረበ በ30 ቀናት ውስጥ ካሳ ሊከፈለዉ ይገባል ብለዋል፡፡

በወርሃ ሰኔ በኮቪድ -19 ሰለባ ለሆኑ ቤተሰቦች ካሳ እንዲከፈል የፍርድ ቤት ጣልቃ ገብነት እንዲኖር መጠየቁ ይታወሳል፡፡መንግስታት በክፍያው ላይ ምን ወጪ ሊፈጽም እንደሚችል እስካሁን በግልጽ አልተነገረም፡፡በነሐሴ ወር በጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የሚመራው የብሔራዊ የአደጋ አስተዳደር ባለሥልጣን ወረርሽኙ ባለመጠናቀቁ ለካሳ ምን ያህል ገንዘብ መመደብ እንዳለበት ግልፅ አይደለም ሲሉ ለግዛቶች ደብዳቤ መጻፋቸዉ አይዘነጋም፡፡

እንደ ካርናታካ ያሉ አንዳንድ ግዛቶች በኮቪድ -19 ህይወታቸዉን ላጡ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸዉ ቤተሰቦች ከፍተኛ የተባለዉን የ100,000 ሩፒ ካሳን አዉጀዋል፡፡

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *