መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 28፤2014-ኔቶ ስምንት የሩሲያ ዲፕሎማቶች ሲሰልሉ ነበረ በሚል ማባረሩን አስታወቀ❗️

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን በምህጻረ ቃሉ ኔቶ የስለላ መኮንኖች ሆነው በድብቅ እየሠሩ ነው ያላቸዉን ስምንት የሩሲያ ዲፕሎማቶችን አባሯል፡፡ ወታደራዊ ጥምረት የሆነዉ ኔቶ በብራስልስ ዋና መሥሪያ ቤቱ የሚሠሩ የሩሲያ ልዑክ ብዛትን ወደ 10 ዝቅ አድርጎታል።

ኔቶ በ2018 በሳሊስቤሪ የስለላ መርዝ ምክንያት ሰባት የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ከተልዕኮው ካባረረ በኋላ እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ ሲወስድ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። እርምጃዉን ተከትሎ የሩስያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ግሩኮ ምዕራባዉያን ከሞስኮ ጋር ያለውን የዲፕሎማሲያዊ የግጭት ፖሊሲ ቀጥለዉበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ግን የኔቶ ዋና ጸሐፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ ይህ ውሳኔ ከማንኛውም የተለየ ክስተት ጋር የተገናኘ አይደለም ፣ በአይናችን እንዳየነዉ የሩሲያ መጥፎ ተግባር ሲጨምር ጠንቃቃ መሆን አለብን ሲሉ ተናግረዋል። እ.ኤ.አ ከ2014 አንስቶ ሩሲያ የዩክሬይን ግዛት የነበረችዉን የክራይሚያ ባሕረ ገብ መሬት ከያዘች በኋላ በኔቶ እና በሞስኮ መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሯል፡፡

አንድ የኔቶ ባለሥልጣን አስቀድመዉ ዲፕሎማቶቹ ያልታወቀባቸዉ የሩሲያ የስለላ ኃላፊዎች ናቸው ብለዉ ነበር፡፡በሩሲያ ፓርላማ የታችኛው ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሊዮኒድ ስሉስኪ በዲፕሎማቶቹ ላይ የቀረበውን ውንጀላ መሠረተ ቢስ በማለት የኔቶ እርምጃ ግንኙነታችንን የበለጠ ያሻክረዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በሚኪያስ ጸጋዬ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *