መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 17፤2014-ሞሮኮ በኮቪድ ምክንያት ወደ ፈረንሳይን የሚደረግ በረራን ልታስቆም ነው፤ አንዳንድ ሀገራትም ድንበራቸዉን መዝጋት ጀምረዋል

ሞሮኮ በኮቪድ ምክንያት ወደ ፈረንሳይን የሚደረግ በረራን ልታስቆም ነው፤ አንዳንድ ሀገራትም ድንበራቸዉን መዝጋት ጀምረዋል

በኮሮና ቫይረስ ወረርሸሽኝ ምክንያት ሞሮኮ ከዛሬ እኩለ ሌሊት ጀምሮ ወደ ፈረንሳይ የሚደረገውን በረራ እንደምታግድ አስታዉቃለች፡፡የሞሮኮ መንግስት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ሀገሪቱ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር አስቀድማ ያስመዘገበችውን ውጤት ለማስጠበቅ ነው ተብሏል።

በፈረንሣይ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረ የሚገኝ ሲሆን በትላንትናዉ እለት ብቻ 33,464 ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸዉ ሪፖርት ተደርጓል ።የፈረንሣይ መንግሥት አምስተኛውን ማዕበል ለመግታት አዳዲስ የክትባት መጠኖችን መስጠትን ጨምሮ ወረርሽኙን ለመከላከል ያስችላል ያለዉን እርምጃ አስታውቋል።የበረራ እገዳው የጠበቀ ግንኙነት ባላቸው የሁለቱ ሀገራት የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል በደቡብ አፍሪካ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ልዉጥ ዝርያ ከተገኘ በኋላ ሀገራት የጉዞ ገደቦችን እያጠናከሩ ይገኛል፡፡እንግሊዝ ፣ ሲንጋፖር እና ጃፓን ጥብቅ የለይቶ ማቆያ እርምጃ እና ከደቡብ አፍሪካና ከቀጠናዉ ሀገራት በረራዎች እንዳይደረጉ ከልክለዋል፡፡የአውሮፓ ህብረት ከደቡብ አፍሪካ ቀጠና የሚመጡ በረራዎችን ለመከልከል ሀሳብ አቅርቧል ።

ዩናይትድ ኪንግደም እና ኔዘርላንድስ ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋና ፣ናምቢያ የዚምባቡዌ፣ኢስዋቲኒና ሌስቶ የሚያደርጉትን በረራ አቁመዋል፡፡

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *