በኢትዮጲያ አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ ኦሚክሮን እንዳይከሰት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጥንቃቄ ያድርግ ተባለ፡
የዓለም ጤና ድርጅት አዲሱን የኮቪድ-19 ዝርያ ‘ኦሚክሮን’ አሳሳቢ መሆኑን ማስታወቁን ተከትሎ በኢትዮጵያም እንዳይከሰት የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥንቃቄዎች ማድረግ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
የአዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከደቡብ አፍሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት የተደረገ ሲሆን በቦትስዋና፣ በቤልጂየም፣ በሆንግ ኮንግ እና በእስራኤል መገኘቱ ኢንስቲትዩቱ ለብስራት ሬድዮ የላከዉ መረጃ ያሳያል።
ኢንስቲትዩት አዲሱ የኮቪድ-19 የኦሚክሮን በኢትዮጲያ እንዳይከሰት እና የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ እያንዳንዱ ግለሰብ ፤ ቤተሰብ ፤ ሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፤ የሐይማኖት ተቋማት ፤ ሲቪክ ማህበራት ፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፤ የጤና ባለሙያዎች ፤ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታትና ለመቆጣጠር ከዚህ በፊት ህብረተሰቡ ያደርገው ከነበረው በበለጠና በተጠናከረ ሁኔታ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ማስክን ሁልጊዜና በአግባቡ ማድረግ ፤ የእጅ ንፅህናን መጠበቅ ፣የኮቪድ-19 ክትባቶችን መከተብ፣ አላስፈላጊ መሰባሰቦችን መቀነስ እንደሚገባ አሳስቧል ፡፡
በትግስት ላቀዉ