የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ለባለሙያዎች ፍቃድ መስጠት የሚያስችለውን በአዋጅ የተሰጠኝን መብቴን ተከልክያለሁ ሲል አስታወቀ❗️
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በ1992 ዓ.ም በወጣው አዋጅ መሰረት ከቅርስ ጋር ተያይዞ የሚደርገውን ማንኛውንም የጥበቃ እና እንክብካቤ ሞያዊ ፍቃድ ይሰጣል የሚል ሲሆን ይህን ተከትሎ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱም የሞያ ብቃት ማረጋገጫ ለመስጠት የሚያስችለውን መመሪያ አዘጋጅቷል፡፡
በተለይ ደግሞ ከሚዳሰሱ ፣ ከሚንቀሳቀሱ ቅርሶች እና ቅርስ ሆኖ የተመዘገቡ የግድግዳ ላይ ስእሎችን ታሳቢ ያደረገ መመዘኛ መስፈርት ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ለመግባት ቢሞከርም መብታችንን መጠቀም አልቻልንም ሲሉ በባለስልጣኑ የቅርስ ጥገና እና እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ጌታቸው በተለይ ለብስራት ሬዲዪ ተናግረዋል፡፡
ይህም የሆነው ባሳለፍነው አመት እንደሃገር የሚሰሩ ኮንስትራክሽን ነክ ክዋኔዎች በተመለከት እና የብቃት ማረጋገጫ የመስጠት ሃላፊነቱ ወደ ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በመዞሩ የተነሳ ነው ብለዋል፡፡ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መብቱን ልጠቀም ቢል ቅድሚያ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሩም የተሰኘ ማረጋገጫ ሊሰጠው ይገባል ያሉት ኃላፊዋ ይህንን ሩም የተሰኘ ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም የቅርስ ጥገናም ቢሆን ኮንስትራሽን ነው በሚል ጥያቄአቸው ተቀባይነት ማግኘት አልቻለም፡፡
በኮንስትራክሽን ሚኒስትር ውስጥ የሃላፊዎች ዝውውር በመደረጉ እስካሁን የፍቃድ ሂደቱን ማጽደቅ ያለተቻለ ሲሆን አሁንም ለተሾሙት ሃላፊዎች በድጋሜ ጥያቄውን መቅረቡን ወ/ሮ ሰላማዊት አንስተዋል፡፡የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ተጠሪነቱ ለባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር በመሆኑ ጥያቄዎን ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አቅርቧል፡፡
ውሳኔ የመሰጠት ሂደቱ በመጓተቱ ምክንያት ስራዎች እየተሰሩ ያሉት ባለስልጣን መስሪያቤቱ ባሉት ውስን ባለሙያዎች ብቻ በመሆኑ ጥበቃ እና እንክብካቤ ማግኘት የሚገባቸው ቅርሶች ዋጋ እያጡ ይገኛሉ ሲሉ ወ/ሮ ሰላምዊት ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
ቤተልሄም እሸቱ