
የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር በሀገሪቱ አንድ ጦር ከመቋቋሙ በፊት ምርጫ እንዳይካሄድ አስጠንቅቀዋል።ባለፈው ወር ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር በ2023 የሽግግር ጊዜ ማብቂያን ተከትሎ ምርጫ እንደሚካሄድ ማስታወቃቸዉ ይታወሳል፡፡
በዋና ከተማዋ ጁባ ለፓርቲያቸው አባላት ንግግር ያደረጉት ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር የተዋሃደ የጦር ሃይል ከሌለ ለምርጫው ደህንነት ከየት ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ተቀናቃኞቹ ፕሬዝዳንት ኪር እና ምክትላቸዉ ማቻር ያላቸዉ ግጭት እንዲያበቃ ባለፈው 2020 አመት የካቲት ወር ላይ የአንድነት መንግስት በመመስረት 83,000 ወታደሮቻቸዉን የያዘ አንድ ሰራዊት ለመመስረት ስምምነት ላይ መድረሳቸዉ ይታወሳል፡፡
ማቻር ምርጫ ከመደረጉ በፊት እንዲሟሉላቸው የሚፈልጓቸውን ሌሎች ሶስት ሁኔታዎች ዘርዝረዋል።ከጎረቤት ሀገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች መመለስ፣ አገር አቀፍ የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ እና ቋሚ ህገ መንግስት እንዲኖር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ምክንያቱም ነጻ፣ፍትሃዊ እና ተአማኒ ምርጫ እንፈልጋለን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2013 በኪር እና ሚስተር ማቻር መካከል የነበረዉ አለመግባባት በሀገሪቱ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ግጭቱ ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አስገድዷል፡፡ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ከሱዳን ያገኘችው እ.ኤ.አ በ2011 ነበር።
በስምኦን ደረጄ