መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 1፤2014-የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሆቴልና መስተንግዶ ኢንዱስትሪ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ አስመረቀ !

ባንኩ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቱን በማዘመን እና ተደራሽነቱን በማስፋት አገልግሎት ሰጪዎችንና ደንበኞችን የዘመናዊ የክፍያ ስርዓት ተጠቃሚ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል። በዛሬው እለትም የዲጂታል ባንኩን ለማዘመን ከኤግል ላየን ሲስተም ቴክኖሎጂ ኋ/የተ/ማህበር ጋር በመተባበር አዲስ የቴክኖሎጂ ውጤትን አስተዋውቋል።

ይኸውም በኢትዮጵያ የሆቴልና መስተንግዶ ኢንዱስትሪ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ (Get Rooms) ፣ የኦንላይን አገልግሎት መክፈያ (Get Free) እንዲሁም (Hotel Bidding Service) ሶስት የኦንላይን አገልግሎት መስጫ አማራጮችን በአንድ ላይ የያዘ አዲስ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አስመርቋል።

የቴክኖሎጂው ስራ ላይ መዋል የሆቴል ዘርፍን በከፍተኛ ደረጃ የሚያዘምንና የሀገር ውስጥና የውጭ ምንዛሪ ግኝት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ በአይነቱ ልዩ የሆነ የቴክኖሎጂ ውጤት ስራ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ተናግረዋል። ባንኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን እያደረገ ያለውን ተሳትፎ እያጠናከረ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት በኢትዮጵያ 57በመቶ ደርሷል። ይህ አሀዝ ከጎረቤት ሀገራት ሲነፃፀር እምርታ እያሳየ ስለመሆኑና በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ኬንያ 98በመቶ በዲጂታል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ደንበኞች ተጠቃሚ ማድረግ እንደመቻሏ ቀሪ ስራዎች እንዳሉብን ማሳያ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ተናግረዋል።

ይህ ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴክኖሎጂ ውጤት በቀላሉ የዓለምዓቀፍ እና የሀገር ውስጥ የበረራ ተጠቃሚዎች ከሆቴሎች ጋር በቀላሉ እንዲገናኙ ከማድረግ ባሻገር ፣ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በመቀነስ የጥቁር ገበያን ለመከላከል የሚያግዝ ፣ የውጪ ገበያውን የሚያሳልጥ መሆኑንም የኤግል ላየን ሲስተም ቴክኖሎጂ መስራችና ስራ አስፈፃሚ አቶ በእርሱፈቃድ ጌታቸው ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል።

ከ 33ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ንግድ ባንክ ፤ ከ 801ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ፣ ከ836 ቢሊዮን ብር በላይ ደግሞ በማበደር የደንበኞችን አጋርነት ማሳየት ችሏል።

እንዲሁም ከ 37ሺህ በላይ ቋሚና ፣ ከ27ሺህ በላይ የኮንትራት ሰራተኞች በውስጡ አቅፏል። ንግድ ባንኩ አጠቃላይ ሀብቱ 1.08 ትሪሊዮን ብር መድረሱም በመርሀ ግብሩ ተጠቅሷል።

6.2 ሚሊዮን የሚደርሱት ደንበኞች በሞባይል በየእለቱ ከባንኩ ጋር ሲገናኙ 22ሺህ የሚሆኑት በኢንተርኔት አገልግሎት አማካኝነት ተጠቃሚ ናቸው። 1700 ቅርጫፎች ሲኖሩት ፣ ከ3000 በላይ የኤቲኤም ማሽኖች በባንኮች ፣ በሆቴሎች እና በሌሎች የገበያ ማዕከላት አሉት።

የምርቃት ስነ ስርዓቱ የቱሪዝም ፕሮሞሽንና ግብይት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ፣ የዘርፉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ፣ የሆቴል ባለቤቶች በተገኙበት ተካሂዷል።

በሚኪያስ ፀጋዬ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *