መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 5፤2014-መንግስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የጠራው ስብሰባ ፖለቲካዊ አላማ የያዘ ነው ሲል ገለፀ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የጠራው ልዩ ስብሰባ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያለው ነው ሲል የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የምክር ቤቱ አባላት የተጠራውን ስብሰባ ውድቅ እንዲያደርጉም ሚኒስሩ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ የጠራው ስብሰባ ድርጅቱና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያደረጉት የጣምራ ምርምራና መንግስት የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ እያደረገ ያለውን ጥረት የገፋ መሆኑን አስታውቋል።

በጥምር ሪፖርቱ የቀረቡ ምክር ሀሳቦችን መንግስት ተቀብሎ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታውሷል።ይህ ባለበት ሁኔታ በምክር ቤቱ የተጠራው ልዩ ስብሰባ ፍላጎት ፖለቲካዊ አላማ ለማሳካት እንደሆነ በግልጽ መረዳት እንደሚቻል አመልክቷል።

አንዳንድ አገራት ምክር ቤቱን ለራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ አድርገው መጠቀማቸው ኢትዮጵያን እንዳሳዘናት ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ምክር ቤቱን በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሕወሃት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች የፈፀማቸውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ላይ ምርምራ ማድረግ ሲጠበቅበት በተወሰኑ አገራት የፖለቲካ ፍላጎት ምክንያት ያን አለማድረጉን አስታውቋል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ይህን ያልተገባ አካሄዱን በአስቸኳይ ማቆም እንዳለበት አመልክቷል።

የምክር ቤቱ አባል አገራትም ይህንን የተወሰኑ አገራትን የፖለቲካ አላማ ለማስፈጸም የተጠራውን ልዩ ስብሰባና ውጤቱን በመቃወም ውድቅ እንዲያደርጉት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል።የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም አቀፉ ህግ መሰረት ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር፤ ለማስከበርና ለማሟላት ያለውን ቁርጠኝነት ለሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባላትና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዳግም ለማረጋገጥ ይወዳል ሲልም በመግለጫው አስገንዝቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *