
የሱዳን የጸጥታ ሃይሎች በዋና ከተማዋ ካርቱም ሲቪል አገዛዝ ሀገሪቱን እንዲመራ የሚጠይቁ ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ መተኮሱ ተሰምቷል፡፡ ለተከታታይ ሳምንታት በሺዎች የሚቆጠሩ የተቃዋሚ ሰልፈኞች በፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግስት አቅራቢያ የሚያደርጉትን መሰባሰብ አሁንም አጠናክረዉ ቀጥለዋል፡፡
ሰልፈኞቹ በጥቅምት ወር በመንግስት ግልበጣ የሲቪል አባላት ከስልጣን መውረዳቸዉን ይቃወማሉ።ባለፈው ወር ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክን ወደ ስራቸው የተመለሱበትን ስምምነትም በማዉገዝ ሴራ ሲሉ ያጣጥላሉ፡፡
በካርቱም በትላንትናዉ እለት የተቃዋሚ ሰልፈኞች የሱዳንን ሰንደቅ በማውለብለብ ሲቪል አገዛዝ የህዝብ ምርጫ ነው እንዲሁም ህዝቡ የበለጠ ጠንካራ ነው በማለት ድምጻቸዉን መካሄዱን እማኞች ተናግረዋል።
ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ሀገሪቱን ወደ ዲሞክራሲ ለመምራት የተቋቋመውን የወታደራዊ እና የሲቪል ሉዓላዊ ምክር ቤት በትነው በመላዉ ሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸዉ ይታወሳል፡፡ነገር ግን እርምጃው ህዝባዊ ተቃውሞ እና አለም አቀፍ ውግዘት በማስከተሉ የገዢው ምክር ቤት መሪ የሆኑት አል-ቡርሃን ባለፈው ወር ሃምዶክን ወደነበሩበት እንዲመልሱ አስገድዷቸዋል። በሀምሌ 2023 ምርጫ ለማካሄድ እና ስልጣንን ለተመረጠዉ የሲቪል መንግስት ለማስረከብ ቃል ገብተዋል፡፡
በስምኦን ደረጄ