መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 5፤2014-የአንጎላ ፕሬዝዳንት ረሃብ አንጻራዊ ነዉ ሲሉ አስተያየት መስጠታቸዉ በህዝባቸዉ ዘንድ ቁጣ ቀሰቀሰ

የአንጎላ ፕሬዝዳንት ጆዋ ሎሬንሶ በሀገሪቱ ያለውን የረሃብ ችግር ዝቅ አድርገዉ የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል፡፡በቴሌቭዥን መስኮት ፕሬዝዳንት ሎሬንሶ ለፓርቲያቸው ደጋፊዎች ባስተላለፉት መልእዕክት ላይ እንደተስተዋለዉ ከሆነ ምንም እንኳን የፖለቲካ ተቃዋሚዎች በሀገሪቱ ስላለው ረሃብ ሁልጊዜ ቅሬታ ቢያሰሙም “ረሃብ አንጻራዊ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

ሎሬንሶ ፓርቲያቸው ለአመታት በመንግስትነት ቢቆይም ድህነትን እና ረሃብን መቋቋም አልቻለም ለሚለው ትችት ምላሽ ሰጥተዋል። ተቃዋሚዎቻችን በጠዋት እና በማታ ነቅተው ረሃብ፣ረሃብ፣ረሃብ የሚል መዝሙር ይዘምራሉ ነገር ግን ረሃብ ሁሌም አንጻራዊ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 8,500 ህጻናት በአንጎላ በረሃብ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡የሎሬንሶ አስተያየት ውዝግብ ያስነሱበት አንዱ ምክንያት ይህ ሆኗል፡፡

በአንጎላ እዉቅ የኃይማኖት አባት የሆኑት ቄስ ጃሲንቶ ፒዮ ዋከሳንጋ በፕሬዝዳንቱ ንግግር መደናገጣቸዉን በመግለጽ ” አንጻራዊ ረሃብ የሚባል ነገር የለም፣ አንጎላ ውስጥ ፍጹም ረሃብ አለ” ሲሉ ተናግረዋል።

በመስከረም ወር የመንግስታቱ ድርጅት የአለም ምግብ ፕሮግራም በደቡባዊ አንጎላ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸዉን በመግለጽ፤ ምክንያቱ ደግሞ በ40 ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ በሀገሪቱ ማጋጠሙ መነገሩ ይታወሳል፡፡

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *