
ሽብርተኛው የህውሃት ቡድን አባላት በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ ሰርገው ለመግባት ቢሞክሩም ጥረታቸው እየከሸፈ እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል ፡፡
እነዚሁ የሽብር ቡድን አባላት የተለያዩ አልባሳትን እየለበሱ መታወቂያ እየያዙ ወደ ከተማዋ ዘልቀው በመግባት ሽብር ለመፍጠር ቢሞክሩም በነዋሪዎች እና በፀጥታ ሃይሉ ጥምረት እንቅስቃሴያቸውን ማክሸፍ ተችሏል ሲሉ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የቴክኒክና ሙያ ልማት ኢንተርፕራይዝ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ አካሉ ወንድሙ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል።
ከእነዚህም ውስጥ የደህንነት ሰው ነኝ በሚል በከተማዋ ሁከት ለመፍጠር የሞከረውን ግለሰብ ጨምሮ የሽብር ቡድኑን መታወቂያ የያዙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሃላፊው በተጨማሪነት ለጣቢያችን ተናግረዋል ፡፡
በተጨማሪም በከተማዋ ጤናማውን የንግድ ስርዓት ለማናጋት የሞከሩ 10 ነጋዴዎች በቁጥጥር ስር ውለው በማስጠንቀቂያ ከታለፉ አንስቶ የገንዘብ መቀጮ የተወሰነባቸው እና የንግድ ተቋሞቻቸው እንዲታሸጉ የተደረገባቸው ይገኛሉ ሲሉ አቶ አካሉ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል ፡፡
በደብረ ብርሃን ሰርጎ ገቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ ህግ ፊት እንዲቀርቡ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ሲሉ ሃላፊው ጨምረው ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል ፡፡
ናትናኤል ሀብታሙ