መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 12፤2014-በሽብርተኛዉ ህወኃት የወደመዉ የቦሩ ሜዳ አጠቃላይ ሆስፒታል መሰረታዊ የህክምና አገልግሎቶችን መስጠት ጀመረ

አሸባሪው የህወኃት ቡድን በወራት ውስጥ ያወደመውን የቦሩ ሜዳ አጠቃላይ ሆስፒታል በሶስት ቀናት ውስጥ መሰረታዊ የህክምና አገልግሎቶችን ስራ እንዲጀምር ማድረጉን የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻለይዝድ ሆስፒታል አስታውቋል ፡፡ በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ከፍተኛ ውድመት ለደረሰበት የቦሩ ሜዳ አጠቃላይ ሆስፒታል ወደ ስድስት ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የህክምና ግብዓቶች እና መድሃኒቶች ድጋፍ በማድረግ አጠቃላይ ሆስፒታሉ መሰረታዊ የህክምና አገልግሎቶችን ስራ እንዲጀምር ማድረግ መቻሉን የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ታምሩ አሰፋ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘው የቦሩ ሜዳ አጠቃላይ ሆስፒታል በአሸባሪው የህወሃት ቡድን እጅግ ከፍተኛ የሆነ የንብረት ውድመትና ዝርፊያ የተከናወነበት በመሆኑ ከጤና ሚንስቴር በወረደ አቅጣጫ መሰረት ይህንን ተቋም መልሶ ለማቋቋም ያስችል ዘንድ የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ባለሙያዎችን ወደ ቦታው ይዞ በመጓዝ በሁለት ምዕራፍ በበላይነት አጠቃላይ ሆስፒታሉን ስራ ለማስጀመር ሃላፊነት ተሰጥቶት የመጀመሪያውን ምዕራፍ ማከናወን ችሏል፡፡

እንደ ዶ/ር ታምሩ ማብራሪያ ከሆነ አሸባሪው ቡድን በወራት ውስጥ ያወደመውን ሆስፒታል በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ሙሉ ለሙሉ በማፅዳት መሰረታዊ የሆኑትን የማዋለጃ፤ የድንገተኛ ቀዶ ጥገና እና የድንገተኛ ህክምና አገልግሎቶችን ማስጀመር ተችሏል፡፡በሁለተኛው ምዕራፍ ላይ ከጤና ሚኒስቴር እና አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሃብት ማሰባሰብ በማድረግ በአጠቃላይ ሆስፒታሉ ውስጥ ቀድሞ ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን መልሶ ለማስጀመር መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

አጠቃላይ ሆስፒታሉን መልሶ ስራ ለማስጀመር በተደረገው ተልዕኮ ላይ ውጤታማ ርብርብ ላደረጉት የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ማኔጅመንት አባላት እና ሰራተኞች እንዲሁም የቦሩ ሜዳ አጠቃላይ ሆስፒታል ባልደረቦችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡፡፡የህውሃት አሸባሪ ቡድን ሆስፒታሉ በየዓመቱ እያሳደገ የመጣውን የመሳሪያ አቅም ሙሉ በሙሉ አዉድሟል፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከዚህ ቀደም በአፋር ክልል በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ውድመት ለደረሰባቸው ለዱብቲ እና ካልዋ ሆስፒታሎች የተለያዩ ባለሙያዎችን በመላክ እንዲሁም 3.2 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ትግስት ላቀዉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *