መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 12፤2014-በሽብርተኛዉ ቡደን ህወኃት ከፍተኛ ዉድመት የደረሰበት የአጣየ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርት መስጠት ጀመረ

አጣየ የሚገኘው የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሃገራች ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በርካታ ጥፋቶች ሲደርስበት ቆይቶል፡፡ ይሁን እንጂ ትምህርት ቤቱ ትምህርት መስጠት ካቆመበት ጊዜ ጀምሮ የሽብርተኛዉ የህውሃት ቡድን ታጣቂዎች ለአስራ ዘጠኝ ቀናት ይኖሩበት እንደነበረ የትምህርት ቤቱ ምክትል ርእሰ መምህር የሆኑት አቶ ወንዳፍር ሰብስቤ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

አያይዘውም እንደገለጹት ከሆነ የትምህርት ቤቱ የመማሪያ ቁሳቁሶች ማለትም ኮምፒውተሮች፣ የላብራቶሪ ክፍሎች እንዲሁም መማሪያ ክፍሎች ከጥቂት መቀመጫ ወንበሮች ውጪ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስችል ሁኔታዎች የወደመ ሲሆን በተጨማሪም የተግባር ትምህርት የሚሰጥባቸው ክፍሎችም ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት የማይችሉ በመሆኑ የጽሁፍ ትምህርት ብቻ እንደሚሰጥም ጨምረው ተናግረዋል።

በ1962 ዓ.ም የተመሰረተው ይህ ትምህርት ቤት በርካታ ሙሁራኖችን ያፈራ መሆኑን እንዲሁም በአሁኑ ሰአት አካባቢው ላይ በነበርወ የሰላም እጦት ምክንያት አካባቢያቸውን ለቀው ለሄዱ አስተማሪዎች ጥሪ እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል፡፡ከትላንትና ጀምሮ ለመምህራን ወደ ስራ እንደሚገቡ እና ለተማሪዎቹም ጥሪ እያቀረበ መሆኑን የትምህርት ቤቱ ተቆጣጣሪ የሆኑት መምህር ማሙሽ ሲከፋኝ ከብስራት ሬዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

ጨምረውም የደረሰብን ጉዳት ከፍተኛ ነው ከቁሳቁስ ባለፈ ለተማሪዎቹም ሆነ ለአስተማሪዎች የስነልቦና እገዛ ያስፈልጋቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።

በኤደን ሽመልስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *