መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 12፤2014-የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ በ2013 በጀት ዓመት ከ2.64 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ

በኢትዮጵያ የጥቁር ገበያ እና የኮቪድ ወረርሽኝ የውጪ ምንዛሬ በተፈለገ መጠን እንዳይሰበሰብ እንቅፋት ሆኖ ቢቆይም የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ በ2013 በጀት ዓመት ይህንን ችግር በመቋቋም ከ2.64 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ መሰብሰብ ችሏል፡፡

የኢትዮጲያን ልማት በሚፈለገው ደረጃ ለመደገፍ የሃብት ማሰባሰብ በተለይም ደግሞ የውጪ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ ወሳኝ ቢሆንም ይህ ዘርፍ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጡ ይነገራል፡፡በዘርፉም እየተስተዋሉ ካሉ ዋና ዋና ችግሮች መካከል የጥቁር ገበያ የውጪ ምንዛሬ አንዱ በመሆን እንቅፋት መፍጠሩን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በየአመቱ ኢትዮጲያ ለውጪ ገበያ የምታቀርበው ምርት ቢጨምርም በአለም ገበያ የግብርና ምርቶች ዋጋ መዋዠቅ የውጪ ምንዛሬ ግኝቷን በሚፈለገው ደረጃ እንዳያድግ አድርጓል ሲሉም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማዕከላዊ ሪጅን ፕሬዝዳንት አቶ ኪዳኔ መንገሻ ተናግረዋል፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ እና የውጪ ምንዛሬ ግኝት ለማሳደግ የሚረዱ አዳዲስ አሰራሮችን ባንኩ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛልም ብለዋል ፡፤ከነዚህም መካከል በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር ቤት የሚልኩትን የውጪ ምንዛሬ ለማሳደግ የሚረዱ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ባንኩ ማስታወቁን ብስራት ሬድዮ ሰምቷል፡፡

ከዚህም ጎን ለጎን የላኪዎችና የተቀባዮችን ምቾትና ፍላጎት ለማርካት የሚያስችሉ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል ፡፡በይቆጥቡ ይሸለሙ መርሃ ግብር ዜጎች ከውጪ የሚላክላቸውን ገንዘብ ከባንክ ብቻ እንዲቀበሉ የማበረታታት ስራ በሰፊው እየተሰራበትም ይገኛል ብለዋል፡፡

ቅድስት ደጀኔ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *