መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 12፤2014-ሳዑዲ መራሹ ጥምር ጦር በየመን ኤርፖርት ላይ የአየር ላይ ጥቃት ፈፀመ

በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ጦር በየመን ዋና ከተማ ሰነዓ በሚገኘው አየር ማረፊያ ላይ ትናንት የአየር ላይ ጥቃት ፈጽሟል። ጥምረቱ የአየር ማረፊያው መገልገያዎች ድንበር ዘለል ጥቃቶችን ለመፈጸም ጥቅም ላይ እየዋለ በመሆኑ የአፀፋ ምላሽ መስጠቱን አስታውቋል።

የመን ከ2014 ጀምሮ በአማፂያን እና በመንግስት መካከል የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ትገኛለች።በኢራን የሚደገፉት እና የየመንን አብዛኛውን ግዛት የተቆጣጠሩት የሃውቲ ሃይሎች የሰንዓ አየር ማረፊያን በእጃቸው ካስገቡ አመታት ተቆጥረዋል። አየር ማረፊያው በተባበሩት መንግስታት የሚመራ የሰብአዊ አገልግሎት ማዕከል ሆኖ ቆይቷል።

ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ሰራተኞች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ጥምረቱ አሳስቧል ሲል የሳዑዲ መንግስት ሚዲያ ዘግቧል። ጥቃቱ ወታደራዊ ኢላማ ነው ብሎ በሚቆጥራቸው የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የሳዐዲ መንግስት አስታውቋል።

ጥቃቱ ስድስት ኢላማዎችን መምታቱን ቃል አቀባዩ ብርጋዴር ጀነራል ቱርኪ አል-ማልኪ ገልፀዋል። ከነዚህም መካከል ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለማጥቃት የሚያስችሉ ቦታዎችን፣የሰው አልባ አውሮፕላን ሰራተኞችን ማሰልጠኛ፣የአሰልጣኞች መኖሪያ ቤት ጨምሮ የሰው አልባ አውሮፕላኖችን ማከማቸት ስፍራን እንደሆነ ተናግረዋል።

ጀነራል ቱርኪ አል-ማልኪ በሰጡት መግለጫ የተወሰደው እርምጃ በኤርፖርቱ የመጓጓዣ አቅም ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ አይኖረውም የአየር ክልልን ፣የአየር ትራፊክን እና የመንደርደሪ ስራዎችን አልጎዳንም ሲሉ አስረድተዋል።በሌላ በኩል የሃውቲ ኃይሎች በማዕከላዊዋ ማሪብ ከተማ እና የወደብ ከተማ በሆነችው ሆዴይዳ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን አጠናክረው ቀጥለዋል።

በሚኪያስ ጸጋዬ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *