መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 14፤2014-በአሸባሪው ህወኃት ከወደሙ የጤና ተቋማት መካከል 64 የሚሆኑት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ተባሉ

በአፋር እና በአማራ ክልሎች የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ስራ ለማስጀመር በተደረገ እንቅስቃሴ እስካሁን 64 የሚሆኑ የጤና ተቋማት በድጋሚ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መቻሉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በተመለከተ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የአሸባሪውና ወራሪው የህወኃት ቡድን ወረራ ባካሄዳቸው በአማራ እና አፋር ክልሎች የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት እና ወደ ሥራ ለማስገባት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ በፈፀመው ወረራ የህክምና ተቋማትን ከማውደም ባለፈ የህክምና መሳሪያዎችን እና መድኃኒቶችን እንደዘረፈም ተናግረዋል።

በሁለቱ ክልሎች የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ሥራ ለማስጀመር እና ለማደራጀት በተለያዩ መንገዶች የሀብት ማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። በተጨማሪም ጦርነቱ በጤና ዘርፍ ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ መነገሩን ብስራት ሬድዮ ሰምቷል።

ሚኒስትሯ አያይዘውም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ በመሰራጨት ላይ እንደሚገኝ የገለፁ ሲሆን ኅብረተሰቡ ለኮቪድ 19 ወረርሽኝን የመከላከያ እና የመቆጣጠሪያ መንገዶችን መተግበሩ ላይ ከፍተኛ መዘናጋት እያሳየ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

በትግስት ላቀው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *