መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 18፤2014-ዴዝሞንድ ቱቱ ማናቸው?

ዴዝሞንድ ቱቱ በዓለም ዙሪያ ወዳጅ እና አድናቂዎችን ያተረፉ ሳቢ ፈገግታ ያላቸው የደቡብ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ ነበሩ። ከነጭ-የጥቂቶች አገዛዝ ጋር በሚደረገው ትግል ውስጥ የተሳተፉ፣ ነገር ግን ሁል ላጊዜ ዓላማቸው ፖለቲካዊ ሳይሆን ሃይማኖታዊ የነበር ታላቅ ሰው ነበሩ።

ዴዝሞንድ ምፒሎ ቱቱ እ.ኤ.አ በ1931 በትራንቫአል በተባለች ትንሽ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ከተማ ከድሃ ቤተሰብ ተወለዱ።በልጅነታቸው የህክምና ዶክተር የመሆን ህልም የነበራቸው ቢሆንም ወላጆቻቸው ለህክምና የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን ባለመቻላቸው የተነሳ እልማቸው ሳይሳካ ቀረ።

የአባታቸውን ፈለግ በመከተል የመምህር ስልጠና ወስደው መስራት ጀምሩ።ሆኖም ግን ደካማ የትምህርት ስርዓት ብሎም ጥቁሮችን አግላይ በመሆኑ ስራቸውን እየጠሉት መጡ። በዚሁ የትምህርት ስርዓት ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ እ.ኤ.አ በ1953 የባንቱ ትምህርት ህግ ፀደቀ።ይህ ህግ ይበልጥ ጥቁሮችን በትምህርት ስርዓቱ አግላይ የሚያደርግ በመሆኑ ስራቸውን ትተው የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ኑሮ ለመቀየር እና የዘር ልዩነትን መታገል ጀመሩ።

በአንድ ጳጳስ ምክር በመነሳሳት ዴዝሞንድ ቱቱ ለካህናት የሚሰጠውን ትምህርት ቀሰሙ።እ.ኤ.አ በ1960 በአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን በቅስና ተሾሙ።ዴዝሞንድ ቱቱ ነገረ መለኮትን ለመማር በ1962 ደቡብ አፍሪካን ለቀው ወደ ለንደን አቀኑ። ከአራት ዓመታት ቆይታ በኃላ በነገረ መለኮት በማስተርስ ዲግሪ ለመመረቅ በቁ።

እ.ኤ.አ. በ1975 በጆሃንስበርግ የቅድስት ማርያም ካቴድራል ዲን በመሆን ያገለገሉ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ለመባል የበቁ ሲሆን በ1978 ደግሞ የደቡብ አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት የመጀመሪያው ጥቁር ዋና ጸሐፊ ሆነው ተሹመዋል።

የኖቤል ኮሚቴ ለህዝቦቹ መብት በመታገል ላይ ያላቸውን የነቃ ሀሳብ እና ፍርሃት የለሽ አቋማቸውን አሞካሽቷል። ለሁሉም የአፍሪካ የነጻነት ታጋዮች አንድ የሚያደርጋቸው አካል ተደርገው ይታዩ ነበር። የቱቱ የአመፅ ሞዴል እንደ ትክክለኛው የነጻነት መንገድ ሰላም አምጥቷል ተብሎ ይታመናል።እ.ኤ.አ. በ 1984 የአፓርታይድን ሰላማዊ ተቃውሞ በማምጣት የኖቤል የሰላም ሽልማትን የተቀዳጁ ሲሆን የደቡብ አፍሪካ አናሳ ነጭ አገዛዝን የተቃወሙ አርበኛ ነበሩ።

ለተገፉ ድምፃቸውን በማሰማት የሚታወቁት ዴዝሞንድ ቱቱ እ.ኤ.አ. በ2017 የማይናማር መሪ እና የኖቤል የሰላም ተሸላሚዋ አውንግ ሳን ሱ ኪን በሀገሪቱ የሙስሊም ወገኖች ላይ የተደረገውን ጭፍጨፋ አምርረው ኮንነዋል።በዚያው በ2017 ዓመት መገባደጃ ላይ ዶናልድ ትራምፕ እየሩሳሌምን የእስራኤል ይፋዊ ዋና ከተማ መሆኗን እውቅና የሰጡበትን ውሳኔ በመቃወም “ፈጣሪ አስከፍቷል” ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ ማስፈራቸው ይታወሳል ።

በአፓርታይድ ዘመን በሁለቱም ወገኖች የተፈፀሙ ወንጀሎችን ለመመርመር የተቋቋመውን የደቡብ አፍሪካ የእውነት እና የዕርቅ ኮሚሽን እንዲመሩ በኔልሰን ማንዴላ ዴዝሞንድ ቱቱ ተሹመው ሰርተዋል።የድህረ-አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካን የብዙዎች ሀገር መሆኗን ለመግለጽ የቀስተ ደመና ኔሽን የሚለውን ቃል እንደፈጠሩም ተመስክሮላቸዋል።

ቱቱ የኔልሰን ማንዴላ የረዥም ጊዜ ወዳጅ የነበሩ ሲሆን በአለም ላይ ሁለት የኖቤል የሰላም ተሸላሚዎች ቪላካዚ በተሰኘ በአንድ ጎዳና ላይ ቤት ቀይሰው ለዓመተት ኖረዋል። ደቡብ አፍሪካን አንድ ለማድረግ ይጥሩ የነበሩት ዴዝሞንድ ቱቱ ዜና እረፍታቸው በዛሬው እለት ተሰምቷል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *