መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 21፤2014-በአዉስትራሊያ ካንቤራ የሚገኘው የቀድሞ ፓርላማ ህንጻ በተቆጡ ሰልፈኞች ተቃጠለ

በአዉስትራሊያ ዋና ከተማ ካንቤራ የሚገኘው የሀገሪቱ የቀድሞ ፓርላማ ህንጻ በዛሬዉ እለት ለአቦርጂናል ሉዓላዊነት በተደረገ ሰልፍ ላይ በተቃዋሚዎች የቃጠሎ አደጋ እንደደረሰበት ፖሊስ አስታዉቋል፡፡የቀድሞ የፓርላማ ህንጻ ላይ በደረሰው ቃጠሎ የተጎዳ ሰዉ ባይኖርም በፓርላማዉ በሮች ተቃጥለዋል፡፡

በዚህ መጠን የተቃውሞ ብጥብጥ በአውስትራሊያ ውስጥ የተለመደ ባይሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኮሮና ወረርሽኝ ተከትሎ እንዲህ ዓይነቱ ተቃዉሞ እየተስተዋለ ይገኛል፡፡አንዳንድ ተቃዋሚዎች ራሳቸውን ፀረ-መንግስት እና የሉዓላዊ አቢርጂናል ቡድን አካል መሆናቸውን በሰልፉ ላይ ሲናገሩ ታዛቢዎች ማድመጣቸዉን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን አውስትራሊያ የምትሠራው በዚህ መንገድ አይደለም በማለት ብጥብጡን አውግዘዋል።የአውስትራሊያ ዜጎች በዚህች ሀገር የዲሞክራሲ ምልክትን ሲያቃጥሉ በማየቴ በጣም ጸጽቶኛል ደግሞም አስደንግጦኛል ብለዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ባርናቢ ጆይስ በትዊተር ገፃቸው ላይ ህንፃ ማቃጠል ህጋዊ ተቃውሞ ሳይሆን ወንጀል እና ከባድ ነው ብለዋል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *