መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 21፤2014-በአጣየ ከተማ ቢያንስ የ30 መምህራን የመኖሪያ ቤቶች በሽብርተኛው ቡድን ህወሓት መቃጠሉ ተነገረ

ሽብርተኛው የህውሃት ቡድን በአጣየ ከተማ በቆየባቸው አስራ አምስት ቀናት ውስጥ ከፍተኛ ውድመት ያስከተለ ሲሆን በአካባቢው ነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች የመሰረተ ልማት እንዲሁም የማህበራዊ አገልግሎቶች የሚሰጡ ተቋማት ላይ የንብረት ውድመት እንዲሁም ስርቆት ተፈፅሟል።

ይሁን እንጂ የአጣየ ፖሊስ የተዘረፉን ንብረቶችን ለግለሰቦች እንዲሁም ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አጣርቶ የማስመለስ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን እንዲሁም ከአጣየ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተሰረቁ ሶስት ኮምፒውተሮች የተመለሱ ቢሆኑም ሌሎች ቀሪ ንብረቶችን እስካሁን ማግኘት አለመቻሉም ተገልጿል፡፡

ትምህርት ቤቱ ከጥቂት ቀናት በፊት የመማር ማስተማሩን ሂደት በ 200 መቶ ተማሪዎች የጀመረ ሲሆን በአሁን ሰዓት ሌሎች ተማሪዎችንም ከያሉበት የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ ይገኛል። የትራንስፖርት አገልግሎቱ ወደ ቀደመው እንቅስቃሴው የተመለሰ መሆኑንም የትምህርት ቤቱ ሱፐርቫይዘር የሆኑት አቶ ማሙሽ ሲከፋኝ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡

አያያይዘውም እንደገለጹት እስካሁን በተደረገው የማጣራት ስራ ሰላሳ የሚሆኑ መምህራን መኖሪያ ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን አንድ መምህር እስካሁን ያለበት አለመታወቁንም ገልጸዋል።በከተማዋ ከሚገኙ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች መካከል በቁጥር ባይታወቅም የሞቱ ተማሪዎች ስለመኖራቸውም የትምህርት ቤቱ ሱፐርቫይዘር የሆኑት አቶ ማሙሽ ሲከፋኝ በተለይም ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡

በኤደን ሽመልስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *