መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 21፤2014-ከኢትዮጲያ የተወሰደው የዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ጎራዴ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ይመለሳል

በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሀገር ተዘርፈው የወጡ ወካይ ቅርሶችን በማስመለስ ረገድ የኢትዮጲያ ቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን ከቀደሙት ጊዜያት በተሻለ በዘንድሮ ዓመት ውጤታማ ስራ መስራቱን አስታውቋል ፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዘንድሮ ዓመት ብቻ ከእንግሊዝ እና ኔዘርላንድስ 16 የሀገር ወካይ ቅርሶችን ከአጋር አካላት ጋር በትብብር በመስራት ማስመለስ መቻሉን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕ/ር አበባው አያሌው ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል፡፡

በአሁን ሰዓትም ሌሎች ቅርሶችን ለማስመለስ እየተሰራ እንደሚገኝ የተነገረ ሲሆን ፤ በሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት ሳምንት ጊዜያት ውስጥ የዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ጎራዴን ለማስመለስ ዝግጅት መጠናቀቁን አንስተዋል፡፡

ጎራዴው ከኢትዮጲያ የወጣበት ትክክለኛ ጊዜ እና አጋጣሚ ባይታወቅም ኤርትራ ውስጥ በነበረው የአሜሪካ ጦር ሰፈር በሚገኝ አሜሪካዊ ወታደር አማካይነት ከሀገር እንዲወጣ መደረጉ ተነስቷል፡፡

የቅርሱን ትክክለኛነት የማረጋገጥ ስራ ተሰርቶ በመጠናቀቁ በሚቀጥሉት ጊዜያት ወደ ሀገር ቤት እንዲመጣ ይደረጋል ያሉት ረ/ፕሮፌሰር አበባው ዝርዝር መረጃውን በወቅቱ እናሳቃለን ሲሉ በተጨማሪነት ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም በእንዲህ መልኩ ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱ ሆነ አስቀድሞውኑ ያሉትን ቅርሶች የመጠበቅ እና የመንከባከብ ስራ ላይ ፈተና የሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ በማጥራት መፍትሔ ለማበጀት እየተሰራ እንደሚገኝ ረ/ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ተናግረዋል፡፡

ናትናኤል ሀብታሙ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *