መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 22፤2014-አዲስ ማዕቀብ አሜሪካ የምትጥል ከሆነ ግንኙነታችንን ሊያበላሽ ይችላል ሲሉ ፑቲን አጠነቀቁ

የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለአሜሪካዉ አቻቸው ጆ ባይደን በዩክሬን ጉዳይ ሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀብ መጣል ግንኙነታችንን ሙሉ በሙሉ ወደመፍረስ ሊያመራ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።የሩሲያው ፕሬዝዳንት በትላንትናዉ እለት ከባይደን ጋር ባደረጉት የስልክ ዉይይት እንዲህ ዓይነቱ ማዕቀብ ትልቅ ስህተት ነው ብለዋል ።

ባይደን በበኩላቸዉ ዩክሬን ላይ ለሚደርስ ማንኛውም ወረራ ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿ ቆራጥ ምላሽ እንደሚሰጡ ለፑቲን ተናግረዋል ።ከአሜሪካ ጋር ለመወያየት በሩሲያ የቀረበዉ የስልክ ጥሪ በዚህ ወር ብቻ ሁለቱን መሪዎች ለሁለተኛ ጊዜ እንዲወያዩ አስችሏል፡፡መሪዎቹ ለአንድ ሰዓት ያህል የፈጀ የስልክ ዉይይት አድርገዋል፡፡

ዉይይቱ በዩክሬን ምስራቃዊ ድንበር በኩል ከሩሲያ ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ለማርገብ የተደረገውን የቅርብ ጊዜ ጥረት የሚያሳይ ሲሆን የዩክሬን ባለስልጣናት ከ100,000 በላይ የሩስያ ወታደሮች በድንበሩ አቅራቢያ ይገኛሉ ሲሉ መናገራቸዉ ይታወሳል።

የሩሲያ ጦር መስፈሩ በምዕራቡ ዓለም ስጋትን ፈጥሯል፣ ዩክሬን ጥቃት ከደረሰባት አሜሪካ ፑቲን አይተው የማያውቁትን ማዕቀብ እጥላለሁ ስት በማስፈራራት ላይ ትገኛለች፡፡ሩሲያ በበኩሏ ዩክሬንን ለመውረር እቅድ የለኝም ወታደሮቹ ልምምድ ላይናቸዉ ብላለች። ወታደሮቼን በገዛ መሬቴ በነፃነት ማንቀሳቀስ መብቴ ነው ስትል ሞስኮ ትናገራለች፡፡

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *