መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 26፤2014-አዲስ አበባ ከተማ በህገ ወጥ እርድ የተነሳ በዓመት ከ1.52 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ እንደምታጣ ተነገረ

የአዲስ አበባ ከተማ በየመንደሩ በሚከናወን ህገ ወጥ እርድ ምክንያት ማግኘት የሚገባትን 1.52 ቢሊየን ብር በላይ እንደምታጣ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ተወካይ የሆኑት ወ/ት ርብቃ ማስረሻ ለብስራት ሬዲዩ ተናግረዋል ፡፡

ለመጪው የገና በዓል ድርጅቱ ከ2500 እስከ 3000 የሚሆኑ የዳልጋ ከብቶች እንዲሁም ከ1500 እስከ 2000 ትናንሽ እንስሳት ማለትም በግ እና ፍየል እርድ እንደሚያከናውን ተገልጿል ።

በቄራ ድርጅት ደጃፍ ላይ በሚገኙ ልኳንዳ ቤቶች የበሬ 285 ብር ፣የበግ እና የፍየል 210 ብር እንደሚሸጥ ተነግሯል።

የበዓል ስራዉ ሰፊ የሰዉ ሀይል የሚፈልግ ከመሆኑ አኳያ በሰዉ ሀይል፤ በግብዓት እንዲሁም የስጋ ስርጭት ተሸከርካሪዎችን በበቂ ሁኔታ በማዘጋጀት ለበዓል ስራዉ አስፈላጊዉ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የጠቅላይ ሚንስትሩን ጥሪ በመቀበል ወደ ሀገር ለሚገቡ ዲያስፖራዎች የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ከአዲስ አበባ ልኳንዳ ማህበር ጋር በጋራ በመሆን ከወትሮ በተለየ መልኩ በፍጥነትና በቅልጥፍና ጥራቱን የጠበቀ የእርድ አገልግሎት በማከናወን ለልኳንዳ ቤቶች፤ ለሱፐር ማርኬቶች አገልግሎቱን ለመስጠት ዝግጅታችንን አጠናቀናል ሲሉ የአዲስ አበባ ልኳንዳ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሳህሌ ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *