መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 27፤2014-ሰሜን ኮሪያ ምንነቱ ያልታወቀ የጦር መሳሪያ ወደ ባህር ማስወንጨፏ ተሰማ

ሰሜን ኮርያ ምንነቱ ያልታወቀ የጦር መሳሪያ ወደ ባህር መተኮሷን የደቡብ ኮሪያ መንግስት አስታዉቋል፡፡የጃፓን የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች የጦር መሳሪያዉ መተኮሱን በመናገር በመጀመሪያ የባልስቲክ ሚሳኤል ሊሆን እንደሚችል ቢገልጹም እስካሁን ማረጋገጫ አልተሰጠውም።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሜን ኮሪያ የባልስቲክ እና የኒውክሌር መሳሪያ ሙከራዎችን እንዳታደርግ ክልከላ መጣሉ ይታወሳል፡፡ቅዳሜ በተጀመረዉ አዲሱ የፈረንጆቹ 2022 ዓመት ፒዮንግያንግ ግን የመጀመሪያዉን ሙከራ አድርጋለች።

የደቡብ ኮሪያ እና የአሜሪካ የስለላ ድርጅቶች ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ሙከራዉን በቅርበት እየተነተኑ ይገኛል። ኪም ባሳለፍነዉ ቅዳሜ ባስተላለፉት መልዕከት ፒዮንግያንግ ከኒዉክሌር መሳሪያ ይልቅ በአዲሱ ዓመት በኢኮኖሚ ላይ ታተኩራለች ሆኖም ግን በኮሪያ ልሳነ ምድር ያለውን ዉጥረት ለመከላከል ወታደራዊ አቅሟ ታጠናክራለች ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡

ኪም ይህን የተናገሩት የሰሜን ኮሪያ ገዥ ፓርቲ የዓመቱ ማብቂያ ላይ ባካሄደው ቁልፍ ስብሰባ ላይ ነበር።የጃፓኑ ጠ/ር ፉሚዮ ኪሺዳ ሰሜን ኮሪያ ከ2021 ጀምሮ በተደጋጋሚ የምታደርገዉ የሚሳኤል ሙከራ
በጣም የሚያሳዝን ድርጊት ብለውታል።

በ2021 ሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ መርሃ ግብሯን ያጠናከረችበት ዓመት እንደነበር ይታወሳል ፣ሰሜን ኮርያ በተጠናቀቀዉ ዓመት አዲስ የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ሙከራ እንዲሁም ከባቡር ላይ የሚወነጨፍ ሚሳኤል እና ረጅም ርቀት የሚምዘገዘግ የክሩዝ ሚሳኤል ሙከራ አድርጋለች።

የባልስቲክ ሚሳኤሎች ከክሩዝ ሚሳኤሎች የበለጠ አስጊ እንደሆኑ የሚነገር ሲሆን ከፍተኛ የጦር መሳሪያ የመሸከም አቅም፣ ረጅም ርቀት የሚጓዙ እና በፍጥነት መብረር የሚችሉ ናቸዉ፡፡

በሚኪያስ ፀጋዬ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *